የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት 11ኛ ዓመት እየተከበረ ነው
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ዛሬ ቅዳሜ 11ኛ ዓመቱን ደፍኗል፡፡ የግድቡ ግንባታ ከዛሬ 11 ዓመታት በፊት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ/ም ነበር የተጀመረው፡፡
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም ኢትዮጵያ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ ተጠቃሽ የሆነ ግዙፍ ግድብ መገንባት መጀመሯን በማብሰር በይፋ የመሰረት ድንጋዩን አኑረዋል፡፡
ከዚያም ወዲህ ግድቡ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፏል፡፡ የነበሩበትን እንደመርግ የከበዱ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ተሻግሮ ከወር በፊት የመጀመሪያውን ኃይል ለማመንጨት ችሏል፡፡
ኢትዮጵያውያን ራሳቸው መሃንዲስም የፋይናንስ ምንጭም ሆነው ይገነቡታል የተባለለት ግድቡ 5 ዓመታትን እንደሚፈጅ ነበር በወቅቱ የተገለጸው፡፡ ሆኖም በግንባታው መጓተት በተለይም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በኃላፊነት ወስዷቸው በነበሩ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች መጓተት ምክንያት በተያዘለት እቅድ መሰረት መጠናቀቅ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ለዚህም በግንባታ ፕሮጄክቱ የተስተዋሉ የአስተዳደር እና የብልሹ አሰራር እንከኖች በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፕሮጄክቱን ዋና ስራ አስኪያጅ የኢንጂነር ስመኘውን ህይወት እስከመንጠቅ የደረሱ ሁነቶች አጋጥመው እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ለውጥ እንደመጣ ከሚነገርበት ከ2010 ዓ/ም ወዲህም በግድቡ የግንባታ ፕሮጄክት ተስተውለዋል የተባሉ ህጸጾች ተነቅሰውና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ተቋራጩን እስከመቀየር እንዲሁም የተርባይኖቹን ቁጥር ከ16 ወደ 13 እስከመቀነስ የደረሱ እርምጃዎች ተወስደው ግንባታው ቀጥሎ አሁን አጠቃላይ የግንባታ ስራው 84 በመቶ ደርሷል፡፡
ከግድቡ 13 ተርባይኖች አንዱ የሆነውና ዩኒት 10 በሚል የሚጠራው ተርባይን ስራ ጀምሮ ነው የመጀመሪያው ኃይል የመነጨው፡፡ ዩኒት 10፤ 375 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨቱ ደስታቸውን ሲገልጹ የነበሩት ኢትዮጵያውያንም ግንባታው የተጀመረበትን 11ኛ ዓመት በተለያዩ ስነ ስርዓቶች በማክበርና የተሰማቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ለተጣለበት 11ኛ ዓም እንኳን አደረሰን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን “ እነሆ! . . .ለሺህ ዓመታት ሲፈስ የነበረው የዓባይ ወንዝ ለሃገራችን ሁነኛ የልማት አቅም ለመሆን በሩ የተከፈተበትን ታሪካዊ ዕለት በጋራ ለመዘከር አበቃን!” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
ወሳኝ የግንባታ ሂደቶችን በማለፍ በአሁን ጊዜ ቅድመ ሃይል ወደ ሚያመነጭበት ምዕራፍ እንደተሸጋገረ በመግለጽም ድጋፉ እንዲሁም በሂደቱ የተስተዋለውን “ የፀና ህዝባዊ አንድነት እና ህብረት” አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ጥሪ አቅርበዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የግድቡን የግንባታ እና የድርድር ሂደቶች በቀዳሚነት ሲመሩ የነበሩት የቀደሞው የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር አምባሳደር ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) “ስንመኘው የነበረውን ሃይል የማመንጨት ውጤት ይዘን፤ በቀጣይ 2 ዓመታት ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሌት ከቀን እየሰራን ነው” ዛሬ የግድቡን 11ኛ የግንባታ ዓመት የምናከብረው ብለዋል፡፡
“በመተባበር፣ በመተጋገዝ እና በትጋት ኢትዮጵያን እናለማለን” ሲሉም የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸውን አስቀምጠዋል በማህበረሰብ የትስስር ገጾቻቸው፡፡
ከወራት በፊት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና የህዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪና አማካሪ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተሾመው የነበሩት ኢ/ር ስለሺ በቀለ በቅርቡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡
ግድቡ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ (በ2017 ዓ/ም) ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ ተገንብቶ ኢትዮጵያውያንና ጎረቤቶቿን ማገልገል እንደሚጀምር የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ክፍሌ ሆሮ ከአሁን ቀደም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ ፕሮጀክቱ ከሶስት ዓመታት በኋላ ተጠናቆ የሚጠበቅበትን 5 ሺ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይጀምራል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን አጠቃላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም በእጥፍ የሚያሳድግ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅም የሀገሪቱን 40 በመቶ የሃይል አቅርቦት ይሸፍናል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላይ 4 ሺ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አላት እንደ ኢ/ር ክፍሌ ገለጻ፡፡
የፋይናንስ ምንጭ ሆነው ግድቡን እንደሚገነቡ የተነገረላቸው ኢትዮጵያውያንም ዐይነተ ብዙ የገንዘብና የዐይነት ድጋችን እያደረጉ ነው፡፡ እስካሁንም በአጠቃላይ ከ16 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ደግፈዋል፡፡ አርሶ አደሩም በጉልበቱ ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር እንደሚበልጥ የሚገመት ድጋፍን አድርጓል፡፡ እስካሁን ለግንባታው የወጣው አጠቃላይ ገንዘብ ከ163 ቢሊየን ብር እንደሚልቅም የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ገልጸዋል፡፡
ድጋፉን ለማስቀጠልም 11ኛ የግንባታ ዓመቱን ታሳቢ ያደረገና ከመጋቢት 20 እስከ ሚያዝያ 05 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆይ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት “ግድባችን የአንድነታችን ብርሀን’’ በሚል መሪ ቃል መጀመሩንም የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡