ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ በግድቡ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ተቃወመች
ኢትዮጵያ የዓረብ ሊግ በግድቡ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ተቃወመች
የዓረብ ሊግ ስራ አስፈፃሚ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት ባስተላለፈው ውሳኔ ቅር ኢትዮጵያ ቅር መሰኘቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከትናንት በስትያ የዓረብ ሊግ ግብጽ በናይል/አባይ ዉሀ ላይ ያላትን ታሪካዊ መብት የሚደግፍ እና የኢትዮጵያን የተናጥል ውሳኔ የሚኮንን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣችው መግለጫ ውሳኔውን ሙሉ በሙሉ እንደማትቀበለው ገልፃለች፡፡
ይህ ውሳኔ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ሀቆችን ከግምት ያላስገባና ለአባል ሀገር ዝምብሎ የተሰጠ ድጋፍ ነውም ብላለች፡፡
ኢትዮጵያ ከዓረብ ሊግ አባል ሀገራትና መንግስታት ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ እሴቶች ላይ የተመሰረተ እና ጥልቅ የባህል ትስስር ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
ሊጉ ሉአላዊ ሀገራትን ያቀፈው እነደመሆኑ፣ እውነታዎችን በተገቢው መንገድ በመረዳት የሁሉንም ፍላጎት ያማከለ ውሳኔ ማሳለፍ ነበረበት ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መቆም ይበልጥ እየተቀራረበ በሚገኘው ዓለም ሊጉ ሰላም፣ መረጋጋት እና ትብብርን ለማስፈን ያለውን አቅም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እንዲሁም ተአማኒነት የሚያሳጣው ነው ሲል መግለጫው ያትታል፡፡
ኢትዮጵያ ግልጽ ውይይቶችን በማድረግ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል ሙሉ እምነት እንዳላትም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
ሱዳን ውሳኔውን ባለመደገፏ ያሳየችው አቋም የሚደነቅ መሆኑን ያስታወቀችው ኢትዮጵያ ሱዳን በድጋሚ “ከምክንያትና ከፍትህ” ጎን መቆሟን ገልጻለች፡፡
ኢትዮጵያ የሱዳን መርህን መሰረት ያደረገ አቋም የሰጥቶ መቀበል መፍትሄ በሁሉም አካላት ዘንድ ለማምጣት ያስችላል ብላለች፡፡
ከዚህ በፊት በነበሩት መንግስታትም እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ፍትሓዊ በሆነ መንገድ “ናይልን በመጠቀም የአሁኑንና የወደፊቱን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት” የቆየና የጸና አቋም አላትም ብሏል መግለጫው፡፡
ኢትዮጵያ ከዓረብ ሊግ ጋር ያላትን ትብብር እና በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርባ መስራቷን እንደምትቀጥልም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አስታውቃለች፡፡