የኢትዮጵያ መንግስት እስረኞቹን መልቀቁ የተገለጸው የሱዳኑ ጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ የኢትዮጵያ ጉብኝት ተከትሎ ነው
የጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎን የኢትዮጵያ ጉብኝትን ተከተሎ ኢትዮጵያ 25 ሱዳናዊያንን ከእስር ለቀቀች፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ በኢትዮጵያ የነበራቸውን የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ ካርቱም ተመልሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ 25 ሱዳናዊያን እስረኞችን መፍታቷን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ሱዳናዊያን እስረኞቹ የተፈቱት ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ነው መሆኑን አል ዐይን ከካርቱም ዘግቧል፡፡
እስረኞቹ የተፈቱት ሁለቱ ሀገራት የጋራ ድንበር ጉባኤ ከአንድ ወር በፊት በብሉናይል እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መካከል የሰላም እና የደህንነት ጉባኤ ካደረጉ በኋላ በተስማሙት መሰረት ነው፡፡
ዛሬ የተፈቱት ሱዳናዊያን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ ማረሚያ ቤት ታስረው የነበሩ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ጀነራል ዳጋሎ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በኢትዮ-ሱዳን የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡የጀነራል ዳጋሎ ጉብኝት የኢትዮጵያ እና ሱዳን ወዳጅነት ወደ መቃቃር ከገባ በኋላ አዲስ አበባን የጎበኙ ከፍተኛው ባለስልጣን ናቸው፡፡