የሙርሌ ታጣቂዎች ወደ ጋምቤላ ክልል ዘልቀው በንጹሃን ላይ ባደረሱት ጥቃት ማዘኑን የደቡብ ሱዳን መንግስት ገለፀ
የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን “ጥቃቱ የመጀመርያ ባይሆንም የሁሉም ጉዳት ነው” ብለዋል
ጥቃቱ ከጀርባው ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎት አንደሌለው አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን አስታውቀዋል
የሙርሌ ታጣቂዎች ወደ ጋምቤላ ክልል ዘልቀው በመግት “በንጹሃን ላይ ባደረሱት ጥቃት ማዘኑን” የደቡብ ሱዳን መንግስት ገለጸ።
በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ለአል-ዐይን ኒውስ እንደተናገሩት፤ በሙርሌ ታጣቂዎች በተሰነዘረውና ለንጹሃን ሰዎች ሞትና መቁሰል ምክንያት በሆነው ጥቃት የደቡብ ሱዳን መንግስት አዝኗል።
“ጥቃቱ የመጀመርያ ባይሆንም የደረሰው ጉዳት ግን የሁሉም ጉዳት ነው” ሲሉም አማባሳደር ጀምስ ተናረዋል።
በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ እና የጋምቤላ ንዌሮች መካከል በየጊዜው ታሪካዊ እና ባህላዊ ግጭቶን ማየት የተለመደ መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ የአሁኑ አሳዛኝ ክስትት ተመሳሳይ እንደሆነና “ከጀርባው ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎት” የሌለው መሆኑንም አስረድቷል።
የአሁን ጥቃት በተሸከርካሪ ላይ ያነጣጠረና ከዚህ በፊት ያልተለመደ መሆኑን በተመለከተ ከአል-ዐይን ኒውስ ለቀረበላቸው ጥያቄም አምባሳደሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
“አዎ ታጣቂዎች ተሽከርካሪን (መኪናን) ዒላማ ማድረጋቸው አዲስ ነገር ቢሆንም፤ በተሽከርካሪ ላይ የጦር መሳርያ አለ ብለው ካሰቡ የማያደርጉበት ምክንያት የለም፤ ጥቃቱን ያደረሱትም ለዚህ ሊሆን ይችላል” የሚል ግምታቸውን ሰጥተዋል።
አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን አክለውም፤ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሁለቱም ሀገራት መንግስታት እንደተለመደው በትብብር ይሰራሉም ብሏል።
በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩት የሙርሌ ጎሳዎች ህጻናትን በማገት እና በመውሰድ እንደ ራሳቸው ልጆች አድርገው በማሳደግ ከብቶችን ማስጠበቅ እና ሌሎች ስራዎችን ማሰራት የተለመደ ባህል ነው።
ከቀናት በፊት ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል የገቡ የሙርሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉ የጋምቤላ ክልል የሰላም ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኦቶው አኮት ለአል ዐይን ኒውስ መናገራቸው ይታወሳል።
ታጣቂዎቹ ባደረሱት ጥቃት የስምንት ሠዎች ህይወት ሲያልፍ በአምስት ሠዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷልም ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው ኦቶው አኮት።
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከዓመታት በፊት፤ በኑዌር ዞን እና አኙዋ ዞኖች ገብተው በርካታ ሕፃናትን አፍነው ሲወስዱ፣ ከአንድ መቶ ሰባ በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ማጣታቸው አይዘነጋም።
ታጣቂዎቹ በወቅቱ ከ2 ሺህ በላይ ከብቶችን መዝረፋቸውን የተናገሩት ምክትል ሃላፊው፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ደቡብ ሱዳን በመግባት ታፍነው ከተወሰዱት ሕፃናት መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑትን ከእገታ አስለቅቆ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሱም ይታወሳል።