የ3ቱን ሰልፈኞች ሞት ያረጋገጠው የሱዳን ዶክተሮች ኮሚቴ በርካቶች ለጉዳት መዳረጋቸውንም አስታውቋል
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ተሳትፈውበታል በተባለለት የዛሬው የሱዳን ተቃውሞ ሶስት ሰዎች ተገደሉ፡፡
በካርቱም የተለያዩ አካባቢዎች የወጡ ሰልፈኞችን ለመበተን በማሰብ ወደ አደባባዮች ወጥተው መንገዶችን የዘጉት በሺዎች የሚቆጠሩ የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጋዝን መተኮሳቸው ተሰምቷል፡፡
የጸጥታ አካላቱ ሲተኩሱ እንደነበር ጭምር ያስታወቀው የሱዳን ዶክተሮች ኮሚቴ የሶስቱን ሰልፈኞች ሞት አረጋግጧል፡፡ ኮሚቴው በርካቶች ለጉዳት መዳረጋቸውንም ነው ያስታወቀው፡፡
የጸጥታ አካሉ ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው መግለጫ ጥፋተኞችን ተጠያቂ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ሱዳናውያን ወታደራዊ አገዛዝ ያብቃ በሚል ወደ አደባባዮች መውጣት ከጀመሩ ወራትን አስቆጥረዋል፡፡
ሁኔታዎችን የገመገመው የሃገሪቱ ብሔራዊ የጸጥታና ደህንነት ምክር ቤትም ሽብርተኝነትን ይዋጋል ያለውን ልዩ ኃይል እንደሚያቋቁም አስታውቋል፡፡
በጥርጣሬ ተይዘው ማስረጃ ያልተገኘባቸውን ታሳሪዎች እንደሚለቅም ነው ምክር ቤቱ የገለጸው፡፡
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋጋን በእጥፍ ለመጨመር ታቅዷል መባሉን ተከትሎ የሃገሪቱን የፋይናንስ ሚኒስቴር ውሳኔን በመቃወም ትናንት እሁድ ወደ አደባባዮች ወጥተውም ነበረ፡፡
ይህን ተከትሎም ሚኒስቴሩ የውሳኔውን ተግባራዊነት ለጊዜውም ቢሆን አዘግይቷል፡፡ ሆኖም ይህ ሱዳናውያኑን አላሳመነም፡፡ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ይደረግ በሚልም በሰሜናዊ የሃገሪቱ አካባቢ የሚገኘውና ሃገሪቱን ከግብጽ የሚያገናኘው መንገድ ተዘግቶም ነበር፡፡
በዋጋዎች ላይ የሚደረጉ የትኛውም ዐይነት የጭማሪ ማሻሻያዎች ወይም ድጎማዎችን ለማንሳት የሚደረጉ ሙከራዎች ሁኔታዎችን ይበልጥ እያባባሱ እንደሚገኙም ነው የተነገረው፡፡
በሱዳን ያለው የኑሮ ውድነት መክፋቱን ተከትሎ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ ወደ 400 በመቶ ማሻቀቡን ይነገራል፡፡
በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከሃገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 20 በመቶ ያህሉ ሰብዓዊ እርዳታን ለመሻት ሊዳረጉ እንደሚችሉም ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትንበያው ያመለከተው፡፡
ተመድ የሱዳን የፖለቲካ ሃይሎችን ለማወያየት የሚያስችል ጥረት መጀመሩን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡