አራተኛውን የአፍሪካ ወጣቶች ውድድር ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ተወሰነ
ኢትዮጵያ ከ 2 ወራት በኋላ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ) ጉባዔንም ታስተናግዳለች
በ2022 የሚካሔደው የውድድሩ አዘጋጅነት ከሌሴቶ ተነጥቆ ነው ለኢትዮጵያ የተሰጠው፡
አራተኛውን የአፍሪካ ወጣቶች ውድድር ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ተወሰነ
የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ) እ.ኤ.አ. በ 2022 ሌሴቶ እንድታስተናግድ ተወስኖ የነበረውን አራተኛውን የአፍሪካ ወጣቶች ውድድር ከሀገሪቱ ነጥቆ ወደ ኢትዮጵያ አዛውሯል፡፡
ሌሴቶ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት እያደረገች ባለመሆኑ ውድድሩ ከማሴሩ ወደ አዲስ አበባ መዛወሩን ማህበሩ ስለማሳወቁ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ብሔራዊ ዝግጅት አባል አራያት ራያ ለአል ዐይን እንዳረጋገጡት ኢትዮጵያ ውድድሩን እንድታስተናግድ የተመረጠች ሲሆን ከአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ጋር በወጪ መጋራት እና መሰል ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡
“የ 2022 የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ አዲስ አበባ ከተማ ተሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ለማስተናገድ ቁርጠኛ ነው” ሲል አኖካ በመግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡
ውድድሩን እንድታስተናግድ በ2018 ዕድሉ ተሰጥቷት የነበረችው ሌሴቶ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ላለፉት 2 ዓመታት ምንም ዝግጅት ሳታደርግ ስለመቆየቷ ነው ማኅበሩ የገለጸው፡፡
ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሔደውን 4ኛውን የወጣቶች ውድድር የተነጠቀችው ሌሴቶ በምትኩ በቂ ዝግጅት በማድረግ ከአራት ዓመታት በኋላ በ2026 የሚካሔደውን 5ኛውን የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች እንድታስተናግድ ተወስኗል፡፡
የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች የመላው አፍሪካ ጨዋታዎችን በመተካት በየአራት ዓመቱ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች የሚካሔድ ውድድር ሲሆን ከዚህ ቀደም የተካሔዱትን 3 ውድድሮች ሞሮካ ፣ ቦትስዋና እና አልጄሪያ በቅደም ተከተል አስተናግደዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሁለት ወራት በኋላ በአውሮፓውያኑ ታህሳስ 6 የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ጉባዔን እንደምታስተናግድም ከአል ዐይን ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ብሔራዊ ዝግጅት አባል አራያት ራያ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡