ሁለት ኢትዮጵያውያን በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል
ሁለት ኢትዮጵያውያን በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 11 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በትዊተር ገጻቸው እንዳስታወቁት አሁን ላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 11 ደርሷል፡፡
አዲስ የተለዩ ሁለቱም የቫይረሱ ተጠቂዎች ቫይረሱ ካለባቸው ሀገራት የመጡ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
አንዱ መጋቢት 5/2012 ዓ.ም ከቤልጂየም ወደ ኢትዮጵያ የመጣ የ28 ዓመት ኢትዮጵያዊ ሲሆን ወደ ሀገር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ራሱን ለይቶ የጤናውን ሁኔታ ሲከታተል ቆይቶ ምልክቱ እንደታየበት ሪፖርት ማድረጉን ተከትሎ በተደረገለት ምርመራ በቫይረሱ መያዙ እንደተረጋገጠ ሚንስትሯ ገልጸዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ከዱባይ መጋቢት 10 ወደ ኢትዮጵያ የገባ የ34 ዓመት ኢትዮጵያዊ ሲሆን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰ በተደረገለት የሙቀት ልየታ ምልክት በማሳየቱ ወደ ለይቶ ማቆያ ተወስዶ በተደረገለት ምርመራ ቫይረሱ ተገኝቶበታል፡፡
ሁለቱም ታማሚዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ዶ/ር ሊያ ከዚህ ቀደም ከተለዩ ታማሚዎች መካከልም ስምንቱ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ከታማዎቹ የ85 ዓመት እድሜ ያላቸው አዛውንት ከባድ የሚባል ህመም ያለባቸው ቢሆንም አስፈላጊው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
ከነገ መጋቢት 14/2012 ዓ.ም ጀምሮ ከውጭ የሚገቡ ሁሉም መንገደኞች በስካይ ላይት ወይም በጊዮን ሆቴል ለ14 ቀናት በራሳቸው ወጪ ተለይተው እንዲቆዩ መንግስት ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል።