በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 9 መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 9 መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙት 6 ሰዎች በተጨማሪ 3 የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መገኘታቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት በጋራ ባወጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው፦ አንደኛዋ ግለሰብ ከዚህ በፊት በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠው ግለሰብ ጋር ንክኪ የነበራቸው የ44 አመት እድሜ ያላቸው ጃፖናዊ፣ ሁለተኛዋ ግለሰብ የ85 አመት እድሜ ያላቸው ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ሶስተኛው ግለሰብ ደግሞ መጋቢት 6 ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የ39 አመት እድሜ ያላቸው ኦስትሪያዊ ናቸው።
በኢትዮጵያ የቫይረሱ መኖር ከታወቀበት መጋቢት 4፣2012 ጀምሮ አዲሶቹን ጨምሮ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 9 ደርሷል።
በቫይረሱ ከተያዙት መካከል ሁለቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ ሲሆኑ የ85 እድሜ ያላቸው ኢትዮጵያዊ ታማሚ ግን ከባድ የሚባል ህመም እንዳላቸውና አስፋላጊው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት በማሰብ መንግስት ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ትምህርትቤቶች ለ15 ቀናት ዝግ ሆነው እንዲቆዩና ብዙ ህዝብ የሚሳተፍባቸው ስብሰባዎችም እንዲሰረዙ ወስኖ፣ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ከቫይረሱ ስርጭት ስጋት ጋር በተያያዘ ፍርድቤቶች ከመጋቢት 10-24 በከፊል ዝግ እንደሚሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት አስታውቋል፡፡ከቻይና ውሀን ግዛት የተቀሰቀሰው ቫይረሱ እስካሁን 176 ሀገራትን ያዳረሰ ሲሆን ከ9,000 በላይ ለሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽን ብሎ የፈረጀው ኮሮና ቫይረሱ እስካሁን ከ200,000 በላይ ሰዎችን ማጥቃት ችሏል፡፡