የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት(ኦቻ) “የተዛቡ መግለጫዎች ከመስጠት እንዲቆጠብ” ኢትዮጵያ ጠየቀች
በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ሁለት አውሮፕላኖች ወደ ትግራይ እንዲበሩ ጥያቄ መቅረቡን መንግስት አስታውቋል
የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት(ኦቻ) “የተዛቡ መግለጫዎች ከመስጠት እንዲቆጠብ” ኢትዮጵያ ጠየቀች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት(ኦቻ) የተዛቡ መግለጫዎች ከመስጠት እንዲቆጠብ የኢትዮጵያ መንግስት ጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎችን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሆነ ኦቻ በትግራይ ሁኔታ የተዛቡ መግለጫዎች ሲያወጣ ነበር ብሏል፡፡
መንግስት ኦቻ የሚያከናውናቸውን ገንቢ ያልሆኑ ተግባራት ኢትዮጵያ ከተቋሙ ጋር በፈረንጆቹ ከ1984 አንስቶ የገነባቸውን ግንኙነት የሚሸረሽር በመሆኑ ድርጊቱን በመቃወም ለተመድ ዋና ጸሃፊ ድበዳቤ መፃፉንም አስታውሰዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት የትግራይን ሁኔታ በተመለከተ የህግ ማስከበሩ ዘመቻ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ “ኦቻ የነበረው ሚና እና የሚያወጣቸው የተዛቡ ሪፖርቶች ገንቢ አልነበሩም” ብሎ እንደሚያምንም መንግስት አስታውቋል፡፡
የኦቻ ሪፖርቶች የህወሐትን የተሳሳተ አስተሳሰብን የሚያጠናክር ፣የሚበራታታ እና ለማወደስ የተቀየሰ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በክልሉ ያለውን ሁኔታ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዳ የሚያደርግ ይመስላልም ነው ያለው መንግስት በመግለጫው፡፡
“ኦቻ ፓርላማ በአሸባሪነት የፈረጀውን ህገ-ወጥ ቡድን የትግራይ መከላከያ ሰራዊት/TDF/ እያለ የሚጠራ ተቋም ነው” ያለው መንግስት ከመስል ድርጊቱ እንዲቆጠብ እንዲሁም ለተቋሙ እና ኢትዮጵያ የቆየ ግንኙነት ሲባል የእርምት እርምጃዎች እንዲወስድ ሲልም ጠይቋል፡፡ መግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁምን ካወጀበት አንስቶ ከሰብዓዊ ስራዎች ጋር በተያያዘ በቅርበት እንደሚሰራ በተደጋጋሚ ሲያረጋግጥ መቆየቱነም አስገንዝቧል፡፡
“ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሲቪል ኤቬሽን ባለስልጣን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለው የአየር ክልል ቢዘጋውም፤ መንግስት ከባለፈው ሰኞ አንስቶ በትግራይ ሰብዓዊ እርዳታን ለማዳረስ ፍላጎት ያላቸውን አካላት እገዛ ለሚሹ ሰዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ፈቃድ ሰጥቷል” በማለትም መግለጫው የመንግስት ዝግጁነት አመላክቷል፡፡
“ በትላንትናው ዕለት በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ሁለት መንገደኞች የያዙ አውሮፕላኖች ወደ ትግራይ እንዲበሩ ከቀረበ ጥያቄ ውጭ፤ ሸቀጣ ሸቀጦችን እና መንገደኞች ይዞ ወደ ትግራይ ክልል ለመብረር እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ መንግስት ቀርቦ የተከለከለ ማንኛውም ዓይነት ጥያቄ አለመቀበሉንም መንግስት ያረጋግጣል” ብሏል መግለጫው፡፡
መንግስት መሰል ጥያቄዎች ለማስተናገድም የሰብኣዊ እርዳታ ሰጪዎች መንግስት ባዘጋጀቸው መመርያዎች እና መረጃዎች መሰረት ከውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ፈቃድ ማግኘት አንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡
መንግስት ሁሉም ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ በረራዎች ወደ ትግራይ ከማቅናታቸው በፊት መጀመርያ በአዲስ አበባ ኤርፖርት ሊያርፉ እንደሚገባም አሳውቋል፡፡ከተከለከለው የአየር ክልል የሚመጡ በረራዎችም በተመለከተም ወደ ውጭ ከመሄዳቸው በፊትም ሆነ በሀገር ውስጥ አየር ማረፊያ ወደ ኢትዮጵያ ከመሄድዎ በፊት ማረፍ እንዳለባቸው መግለጫው አስገንዝቧል ፡፡
“በመመርያው እንደተቀመጠውም ሁሉም እርዳታ ሰጪዎች ከበረራ በፊት የበረራ ቁጥር፣የአውሮፕላኑ አይነት፣ የበረራው ዓላማ፣የመንገደኞቹ ማንነት እንዲሁም የካርጎው አይነትን በተመለከተ ዝርዝሮች ማቅረብ እና ማረጋገጫ ማግኘት አለባቸው”ም ነው ያለው መግለጫው፡፡
መንግስት በመንገደኞች የሚያዙ እንዲሁም በካርጎ የሚጫኑ ቁሳቁሶችም ቢሆኑ ከሰብዓዊ እርዳታ ጋር የተያያዙ ለመሆናቸው መንግስት ማረጋገጥ እፈልጋለሁኝም ብሏል፡፡
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳሳት የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ የሚደረጉትን በረራዎች እያደናቀፈ እንደሆነ ተደርገው የሚነዙ ወሬዎችና የሚወጡ ሪፖርቶች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው ያለው መግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት ግን ከሰብዓዊ አርዳታ ሰጪ ተቋማት ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ያረጋግጣል ብሏል፡፡
ከትግራይ ጋር በተያያዘ ተዘጋጁ መመርያዎችን በተመለከተ በቅርቡ ከባለድርሻ አካለት እና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው አካላት ጋር በቅርቡ ውይይት እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡