በትግራይ “እርዳታን በአየር የማዳረስ ተግባር” በቅርቡ የመጀመር ተስፋ እንዳለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም አመላከተ
መንግስት በበኩሉ የእርዳታ አውሮፕላኖቹ አዲስ አበባ ሲያርፉና ሲነሱ ፍተሻ እንደሚያደርግ አስታውቋል
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የመቀሌ እና የሽሬ ኤርፖርቶች እንደገና ሊከፈቱ ይገባል ብሏል
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሚያደርገው የእርዳታ ስርጭትን የቀጠለ ቢሆንም አሁንም ድረስ በመዳረሻዎች ችግሮች እያጋጠሙት እንደሆነ አስታወቀ፡፡
በችግሮቹ ምክንያት የህይወት አድን አቅርቦቶች ስራው “ወደ ኋላ ቀርቷል” መቅረቱንም በትግራይ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ቶሚ ቶምፕሰን ተናግረዋል፡፡
አስተባባሪው በአሁኑ ሰአት በክልሉ የተወሰኑ ዞኖች “ውጊያው መቀጠሉን” እና ውጊያውን ተከትሎ ከ35 በላይ የድርጅቱ ሰራተኞች “መታፈናቸውን”በሳተላይት ስልክ ከመቀሌ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
“የዓለም ምግብ ፕሮግራም ላለፉት 48 ሰዓታት ስራዎቹን አቁሞ ነበር፤ አሁን በተቻለ ፍጥነት በሰሜን ምእራብ ስራዎች ጀምረናል፤ በመጪዎቹ ቅዳሜና እሁድም 40 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች እርዳታ የምናደርስ ይሆናል"ም ብለዋል ቶሚ ቶምፕሰን በቀጣይ በክልሉ ማዕከላዊ ዞን እርዳታ እንደሚያደርሱ በመጠቆም፡፡
ቶምፕሰን፤ በትግራይ ካለው ችግር አንጻር እርዳታውን ለማፋጠን በቀጣዮቹ ቀናት እርዳታዎችን በአየር ማዳረስ የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁኝም ብለዋል፡፡
“አሁን ያለው እውነታ ሰዎች ሞተዋል፣ እየሞቱ ነው እንዲሁም ከወዲሁ መፍትሄ ካላበጀንለት ተጨማሪ ሰዎች የሚሞቱ ይሆናል”ም ነው አስተባባሪው ያሉት፡፡
የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን በበኩሉ በትግራይ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ እየተባባሰ ነው ብሏል፡፡
ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ፍሊፖ ግራንዲ በትግራይ የሚደረገው አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ የማዳረስ ተግባር ማሳደግ ግድ እንደሚል ጠቁሟል፡፡
“የእርዳታ መጠኑን ስርጭት ለማሳለጥ የመቀሌ እና የሽሬ ኤርፖርቶች እንደገና መከፈት፣ የቴሌኮሚኒኬሽን እና የመብራት አገልግሎቶችም ወደነበሩበት መመለስ እንዲሁም ድጋፍ የሚሹ ዜጎች የሚረዱበት ያልተገደበ መዳረሻ እንዲኖር ማስቻል ይገባል”ም ብለዋል ከፍተኛ ኮሚሽነሩ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ጉዳይ መስርያ ቤቱ በኩል ዛሬ በሰጠው መግለጫ ለትግራይ የሚደረገውን እርዳታ በተገቢው መንገድ እንዲዳረስ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና ክልሉን ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል፡፡
አሁን ላይ የሰብአዊ መብት ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች መጥተው ማገዝ የሚፈልጉ አካላት ይህንን እንዲያደርጉ ቀለል ያለ ቪዛም እንደሚዘጋጅላቸውም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ሬድዋን ሁሴን የገለጹት፡፡
የእርዳታ አውሮፕላኖች በተመለከተም አውሮፕላኖቹ አዲስ አበባ ሲያርፉና ሲነሱ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውና ከፍተሻ በኋላ መሄድ ይችላሉ ብሏል አቶ ሬድዋን፡፡