ኢትዮጵያ ከ11 ዓመት በፊት የፈረመችውን የቤት ሰራተኞች መብት ህግ እንድታጸድቅ ተጠየቀች
በዓለም ላይ 53 ሚሊዮን ሴቶች በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው በመስራት ላይ ናቸው
ኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች መብት ዓለም አቀፍ ስምምነትን ብትፈርምም እስካሁን ህግ አድርጋ አላጸደቀችውም ተብሏል
ኢትዮጵያ ከ11 ዓመት በፊት የፈረመችውን የቤት ሰራተኞች መብት ህግ እንድታጸድቅ ተጠየቀች፡፡
የዓለም ስራ ድርጅት ከ11 ዓመት በፊት በጎርጎሮሲያዊያን አቆጣጠር 2011 ላይ ባካሄደው 100ኛ ጉባኤው የቤት ሰራተኞች መብት ጥበቃዎችን የሚደነግግ ስምምነት በአባል ሀገራቱ አስፈርሟል፡፡
ይህ ስምምነት ሀገራት ተግባራዊ የሚያደርጉት በሀገራቸው ህግ አውጪው አካል ካጸደቀው በኋላ ሲሆን እስካሁን 35 ሀገራት ስምምነቱን የአገራቸው አንድ አካል ሲያደርጉት ከነዚህ ውስጥ አራቱ አፍሪካዊያን ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ስምምነቱን ብትፈርምም እስካሁን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደ አንድ አስገዳጅ ህግ አድርጋ ካላጸደቁ አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) ኢትዮጵያ ይሄንን ስምምነት እንድታጸድቅ ጠይቋል፡፡
ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ሰራተኞችን መላክ የሚችል ፈቃድ ያለው ተቋም እንደሌለ ተገለጸ
እንደ ዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት መረጃ ከሆነ በዓለም ላይ 53 ሚሊዮን ሴቶች በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው በመስራት ላይ ሲሆኑ የቤት ሰራተኞች ለዓለም ሴቶች የስራ እድል ፈጠራ የ7 ነጥብ 5 በመቶ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ይነገራል፡፡
ይሁንና ይህ የቤት ሰራተኝነት የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች ለአድልዖ፣ ያለ እረፍት ረጅም ሰዓት ስራ መስራት፣ ለሰሩት ስራ ተገቢውን ክፍያ አለማግኘት፣ ለአካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ፣ለግዴታ እና ለህገወጥ ስራ ይጋለጣሉ፡፡
እነዚህንና ተጨማሪ ጉዳቶች በቤት ሰራተኞች ላይ እንዳይደርስ የኢትዮጵያ መንግስት ይሄንን ስምምነት እንዲያጸድቅ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ጠይቀዋል፡፡
እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ በኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች የስራ ላይ መብቶች ጥበቃ ከተዘነጉት እና ትኩረት ካልተሰጣቸው የመንግስት ስራዎች አንዱ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች በህግ የሚዳኙት በአጼ ሀይለስላሴ የአስተዳደር ዘመን በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሄር ህግ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ምክንያትም የቤት ሰራተኞች መብት በሚገባ እየተጠበቀ እና ጥበቃ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸው ኢትዮጵያ ከ11 ዓመት በፊት የፈረመችውን ስምምነት እንድታጸድቅ ጠይቀዋል፡፡
ፓስፖርቶችን በህገ-ወጥ መንገድ ሲያዘጋጁ ነበር የተባሉ 10 የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ታሰሩ
በስምምነቱ መሰረት የቤት ሰራተኞች በሳምንት ያልተቆራረጠ የ24 ሰዓታት እረፍት የማግኘት፣ የመደራደር፣ ከስራ አገኛኝ ኤጀንሲ የሚጠየቁ ክፍያዎችን አሰሪው ብቻ እንዲከፍል እና ደመወዝ ሳይቆራረጥ የማግኘት እና ደህንነቱ በተጠበቀ የስራ ስፍራ የመስራት መብቶች አሏቸው፡፡
ኮንፌደሬሽኑ ከቤት ሰራተኞች ጥበቃ አዋጅ በተጨማሪ የጥቃትና ትንኮሳ ስምምነትን እና የስራ ፍልሰተኞች ጥበቃ አዋጅንም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ጠይቋል፡፡