ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ሰራተኞችን መላክ የሚችል ፈቃድ ያለው ተቋም እንደሌለ ተገለጸ
በኢትዮጵያ አሁን ላይ የውጭ ሀገራት ስራ ስምሪት እየተደረገ ያለው ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ብቻ መሆኑን መንግስት ገልጿል
የተባበሩት አረብ ኢምሬት፤ጆርዳን እና ኳታር አሁን ላይ የውጭ ሀገራት ስራ ስምሪት እየተደረገባቸው ያሉ ሀገራት ናቸው ተብሏል
ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ሰራተኞችን መላክ የሚችል ፈቃድ ያለው አንድም ተቋም እንደሌለ መንግስት አስታውቋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ወደ አውሮፓ ሀገራት ስራ እናስቀጥራለን የሚሉ ማስታወቂያዎች ሲሰሙ ይደመጣል።
አንዳንዶቹም በግልጽ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ቢሮ ከፍተው ወደ ካናዳ፤አሜሪካ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ስራ እናስቀጥራለን የሚሉ ማስታወቂያዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀር ያሰማሉ።
- ሳዑዲ በአገሯ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መላኳን ካጠናቀቀች በኋላ አዲስ ቪዛ መስጠት እንደምትጀምር ገለጸች
- ሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ዘመቻ ተጀመረ
በዚያው ልክ ደግሞ በደላሎች ተታለልን በጥሩ ደመወዝ ወደ በለጸጉ ሀገራት ልከን እናስቀጥራችኋለን በሚሉ አማላይ ማስታወቂያዎች ተሸውደን ገንዘባችንን ተበላን የሚሉ ሰዎችን መስማት እየተለመደ መጥቷል።
ይህን ጉዳይ መነሻ በማድረግም አል ዐይን አማርኛ ጉዳዩ ወደ ሚመለከተው አሁን ስሙ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም በቀድሞ ስሙ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴርን ጠይቋል።
በዚህ ተቋም በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት የስራ ውል አጽዳቂ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ገሰሰ ደሬሳ እንዳሉት ወደ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ሀገራት ስራ እናስቀጥራለን የሚሉ ማስታወቂያዎችን እና እሮሮዎችን እንደማንኛውም ሰው እንደሚሰሙ ተናግረዋል።
ይሁንና በአዋጅ 923/2008 ዓ.ም መሰረት የውጭ ሀገራት ስምሪትን የሚያስፈጽመው የእሳቸው ተቋም መሆኑን ተናግረው እስካሁን መስፈርቱን አሟልቶ ወደ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ሀገራት ሰረታኞችን መልምሎ መላክ የሚያስችል ፈቃድ ያለው ኤጀንሲ እስካሁን እንደሌለ ተናግረዋል።
በመሆኑም ወደተጠቀሱት አህጉራት ሰረታኞችን ልከን ስራ እናስቀጥራለን በሚል የሚንቀሳቀሱ ህገወጥ ኤጀንሲዎችን ህግ አስከባሪ የጸጥታ አካላት እንዲያስቆሟቸው አቶ ደሬሳ አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም ዜጋ ለነዚህ ህገወጥ ኤጀንሲዎች ገንዘብ ከመክፈላቸው በፊት ህጋዊነታቸውን እንዲጠይቁ ተጨማሪ መረጃዎችንም ካዛንቺስ ወደሚገኘው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መጥተው እንዲያጣሩም አሳስበዋል።
የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት አዋጅ መሰረት መስፈርቱን የሚያሟላ እና ከዚህ ተቋም የስራ ፈቃድ ያገኘ ኤጀንሲ ወደማንኛውም ሀገር ሰራተኞችን መልምሎ እንዲልኩ ቢፈቅድም እስካሁን ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውጭ ወደ ሌሎች ሀገራት እየተላከ አለመሆኑንም አቶ ገሰሰ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ወደ ተባበሩት አረብ ኢምሬት፤ጆርዳን እና ኳታር ብቻ ሰራተኞች በኤጀንሲዎች አማካኝነት ተመልምለው እየተላኩ መሆኑን ቡድን መሪው ነግረውናል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ1 ሺህ በላይ ኤጀንሲዎች የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ማድረግ የሚያስችላቸውን የስራ ፈቃድ ያገኙ ቢሆንም ብዙዎቹ በኮቪድ 19 ምክንያት ስራ ማቆማቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
ከኮሮና ቫይረስ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት ከሰራተኛ ተቀባይ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት አለመጠናቀቃቸው በውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ስራው ላይ ተጽዕኖ ማሳረፉም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ባለፈው 2013 በጀት ዓመት 37 ሺህ ዜጎችን በኤጀንሲዎች አማካኝነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የላከች ሲሆን በዚህ ዓመት ግን የኮሮና ቫይረስ ጉዳት እየቀነሰ የሚሄድ ከሆነ ከ200 ሺህ በላይ በውጭ ሀገራት ስራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ለመላክ መታቀዱንም ሰምተናል።
የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት እስከ 500 ሺህ ኢትዮጵያዊያን በህጋዊ መንገድ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ይላኩ ነበር።