5 ነጥብ 2 ኪሎሜትር ርዝመት እና 50 ሜትር ከፍታ ያለው የኮርቻ ግድብ የህዳሴ ግድብን መልክ የለወጠ ግዙፍ ግንባታ ነው ተብሎለታል
ኢትዮጵያ በጉባ ሸለቆ ከ12 አመት በፊት ግንባታውን የጀመረችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አሁን አጠቃላይ ግንባታው 93 በመቶ ደርሷል።
የሲቪል ስራው ደግሞ 98 በመቶ ተጠናቋል የሚሉት የግድቡ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፥ የኮርቻ ግድብ (ሳድል ዳም) ግንባታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የኮርቻ ግድብ ምን ፋይዳ አለው?
የኮርቻ ግድብ ሃይል ለማመንጨት የተጠራቀመውን ውሃ አቅፎ የሚይዝ ነው።
5 ነጥብ 2 ኪሎሜትር የሚረዝመው ይሄው ግድብ ከፍታው 50 ሜትር ደርሷል። ይህም 42 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንዲከማች አድርጓል። ግድቡ የያዘው ውሃም ከጣና ሃይቅ በእጥፍ እንደሚበልጥ ነው የተነገረው።
ኢትዮጵያ ስለዚህ የኮርቻ ግድብ ብዙም ስታወራለት አይደመጥም የሚሉት የግድቡ ስራ አስኪያጅ፥ ኮርቻ ግድቡ ባይገነባ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያብራራሉ።
የኮርቻ ግድቡ ባይገነባ፦
- የህዳሴ ግድብ ከፍታ 90 ሜትር፣
- የማምነጨት አቅሙ 1 ሺህ 400 ሜጋዋት፣
- ዋናው ግድብ የሚይዘው ውሃ 11 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ይሆን ነበር ይላሉ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ።
የኮርቻ ግድቡ መገንባት ደግሞ፦
- የግድቡን ከፍታ ወደ 645 ሜትር፣
- ሃይል የማመንጨት አቅሙን ወደ 5150 ሜጋ ዋት፣
- ግድቡ የሚይዘውን ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ከፍ አድርጎታል ብለዋል።
የኮርቻ ግድቡ በ15 ነጥብ 3 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ድንጋይ የተሞላ ሲሆን፥ ውሃ እንዳያሰርግ በኮንክሪት ተሸፍኗል።
በዚህ ረጅም ግድብ ላይ የውሃ ስርገትን፣ የግድቡ ንቅናቄ፣ የመሬት ንዝረትና ሌሎች ጉዳዮችን ለማጥናት የሚያግዙ 1 ሺህ 300 መሳሪያዎች ተገጥመዋል ተብሏል።
የኮርቻ ግድቡ የፈጠረው ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሃይቅ የኢትዮጵያን ቱሪዝም የማነቃቃት ተስፋ ተጥሎበታል።
በቅርቡ 4ኛውን የውሃ ሙሌት ያካሄደው የህዳሴ ግድብ ቀሪ ስራዎች በቀጣይ አመት እንደሚጠናቀቁ ተገልጿል።
የግድቡን የግራና ቀኝ ከፍታ (ከ9 እስከ 10 ሜትር ነው የሚቀረው) የማጠናቀቅ እና ሌሎች የሃይድሮ መካኒካል ስራዎችም የኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ይሻሉ ነው የተባለው።
ተጨማሪ 5 ተርባይኖች በ2016 ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ እየተሰራ ስለመሆኑ የግድቡ ግንባታ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናግረዋል።