ኢትዮጵያ የሩስያ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበች
የኢትዮጵያና የሩስያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀምሯል
በስብሰባው ከዚህ ቀደም በሀገራቱ መካከል የተፈረሙ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚረዳ መሆኑን ሩሲያ አስታውቃለአች
የሩሲያ እና የኢትዮጵያ በይነ መንግስታት የኢኮኖሚ፣ የሳይንስ፣ የቴክኒክ እና የንግድ ትብብር ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በ8ኛው የሩሲያ እና የኢትዮጵያ በይነ መንግስታት ሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ከሩሲያ የመጡ ባለስልጣናት እና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በስብሰባው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የሩስያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በማዕድን እና በሌሎችም የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዶ/ር በለጠ ሞላ አክለውም፤ ሩስያ ኢትዮጵያ በተፈተነችባቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፅናት ከጎኗ በመሆን ለነበራት አጋርነት አመስግነዋል።
ሩስያ በሳይንስ፣ በትምህርትና ሌሎች ዘርፎች ለኢትዮጵያ እያደረገችው ላለው ድጋፍም በማመስገን በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ይቭጌኒ ቴሬኪን፤ ስብሰባው ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር፣ የንግድ ልውውጥን ለማሳደግ እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምክክር የሚደረግበት እንደሆነ ተናግረዋል ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።
ዛሬ መካሄድ የጀመረው በ8ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በሳይንስ፣ ቴክኒክ፣ ኢኮኖሚ እና ንግድ ዘርፎች የቆየውን የሁለትዮሽ ትብብር እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ይረዳል።