ሩሲያ በመረጃ መረብ ደህንነትና በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር እንደመትትሰራ አስታወቀች
ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ሩሲያ ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቃለች
የሩሲያ የዲጂታል ልማት፣ ኮሙኒኬሽንና ብዙሃን መገናኛ ምክትል ሚኒስትር ማክሲም ፓርሺን ኢትዮጵያ ናቸው
ሩሲያ በመረጃ መረብ ደህንነት፣ በዲጂታላይዜሽን እና በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ማሳደግ እንደምትፈልግ አስታወቀች።
በሩሲያ የዲጂታል ልማት፣ ኮሙኒኬሽንና ብዙሃን መገናኛ ምክትል ሚኒስትር ማክሲም ፓርሺን የተመራ ልኡክ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ ነው።
የኢኖቬሽንንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከሩሲያ የዲጂታል ልማት፣ ኮሙኒኬሽንና ብዙሃን መገናኛ ምክትል ሚኒስትር ማክሲም ፓርሺን አና ከልዑካቸው ጋር መወያየጣቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በውይይታቸውም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ሩስያ ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ መደገፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።
በተለይም በዲጂታል ክህሎት እና የመረጃ መረብ ደህንነት ላይ ሩስያ ያላትን የዳበረ ልምድ ኢትዮጵያ መካፈል እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
የሩስያ የዲጂታል ልማት፣ ኮሙኒኬሽንና ብዙሃን መገናኛ ምክትል ሚኒስትር ማክሲም ፓርሺን በበኩላቸው ሩስያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማሳደግ እንደምትሰራ ማረጋገጣቸውን የኢኖቬሽንንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በኤሌክትሮኒክ የመንግስት አገልግሎት፣ በዲጂታል ክህሎት፣ በመረጃ መረብ ደህንነት እና በሌሎችም ዘርፎች በትብብር እንደሚሰሩም ማክሲም ፓርሺን ተናረዋል።
ኢትዮጵያ እና ሩስያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ በተለያዩ የትብብር ዘርፎች በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።