ሱዳን፤ ሙሌቱን ተከትሎ በህዳሴው ግድብ ላይ እርምጃ ትወስዳለች መባሉን አስተባበለች
ካርቱም ጉዳዩን በማስመልከት የሚናፈሰው አሉባልታ እንደሆነ አስታውቃለች
አሁንም አሳሪ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት በሚለው አቋሟ እንደጸናች መሆኗንም ነው የገለጸችው
ሱዳን በሮዜርየስ ግድብ፣ በመስኖ እና በሌሎች የሃይድሮ ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶቿ የውሃ ይዞታ ላይ ችግር ካጋጠመ ሶስተኛ ዙር ሙሌቱ ከሰሞኑ በተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ እርምጃ ትወስዳለች መባሉን አስተባበለች።
የሃገሪቱ የመስኖ እና የውሃ ሃብት ሚኒስቴር ጉዳዩን በማስመልከት መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫው የግድቡ ተደራዳሪ ቡድን የቴክኒክ ኮሚቴ መሪ እንደተናገሩት ተደርጎ በተወሰኑ ሚዲያዎች የቀረበው ዘገባ የተሳሳተ እና ከእውነት የራቀ ነው ብሏል፤ ቡድን መሪው ጉዳዩን በማስመልከት የተናገሩት ነገርም ሆነ የሰጡት መግለጫ እንደሌለም በመጠቆም።
አሁንም የግድቡን ሙሌትና አስተዳደር በተመለከተ ከአሳሪ የሶስትዮሽ ስምምነት ላይ ይደረስ በሚለው አቋሙ እንደጸና መሆኑንም ነው ሚኒስቴሩ የገለፀው።
የናይል ተፋሰስ ሃገራት ለህዝቦቻቸው ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የጋራ ተጠቃሚነት በሌሎች ሃገራት ላይ የጎላ ጉዳትን በማያስከትል መንገድ ተባብረው መስራት ያስፈልጋቸዋልም ብሏል።
ኢትዮጵያ ከሰሞኑ የግድቡን ሶስተኛ ዙር ሙሌት በስኬት በማጠናቀቅ የግድቡን ሁለት ተርባይኖች ስራ ማስጀመሯ ይታወሳል።
በሙሌቱ መጠናቀቅ ማብሰሪያ ስነ ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሙሌቱ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት የሚያገኙ የውሃ መጠን ሳይቀንስ መጠናቀቁን በመግለፅ ግብጽን ጨምሮ ሶስቱም ሃገራት ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ግድቡ በሚይዘው ውሃ ምክንያት 70 ደሴቶች እንደሚፈጠሩ እና ከነዚህ ውስጥ 40ዎቹ አስር ሄክታር ያህል ስፋት እንደሚኖራቸው መናገራቸውም አይዘነጋም።
የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከሱዳን የመስኖ እና የውሃ ሃብት ሚኒስትር ዳው አብደል ራህማን መንሱር እና ከደቡብ ሱዳን የመስኖ እና የውሃ ሃብት ሚኒስቴር ተወካይ አምባሳደር ዴንግ ኦቤድ ጋር ተገናኝተው ጥሩ ጊዜ ማሳለፋቸውን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል። ሆኖም መቼ እና የት እንደተገናኙ ተገናኝተው ምን እንዳወሩም አልገለፁም።