“የኦህዴድ ሹሞች ስልጣንና ሀብትን ወደ አንድ ተረኛ ቡድን ለማዞር ጥድፊያ ላይ ናቸው“ ገለታው ዘለቀ የባልደራስ ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ
ባልደራስ፣ አዲስ አበባ ራስ ገዝ እንድትሆንም እንደሚሰራ አስታውቋል
“ተረኝነት አለ ብሎ የሚያምን ማንኛውም አካል ተጨባጭ ማስረጃ በማምጣት በግልጽ መነጋገር ይቻላል“ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ የፖለቲካ ድርጅት ከመሆኑ በፊት የሲቪክ ማህበር ነበር፡፡ በኋላም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝቶ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ አሁን በእስር ላይ በሚገኙት ጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ የፓርቲው ፕሬዝደንት ናቸው፡፡
የፊታችን ግንቦት መጨረሻና ሰኔ መጀመሪያ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከሚሳተፉና የመወዳደሪያ ምልክት ከወሰዱ 47 ፓርቲዎች መካከል ባልደራስ አንዱ ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ገለታው ዘለቀ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ኃላፊው፣ ፓርቲያቸው ብሔራዊ ሆኖ የመመዝገብ ፍላጎት እንደነበረው ገልጸው “የመመዝገቢያ ጊዜው በመጣበቡ” ምክንያት በአዲስ አበባ ብቻ መወሰኑን አንስተዋል፡፡ አቶ ገለታው፣ ባልደራስ አሁን ላይ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸው ይህም ባልደራስ በአዲስ አበባ ብቻ እንደማይወሰን ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የባልደራስ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ በሸራተን አዲስ ሆቴል ተደርጎ በነበረ ውይይት ላይ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‘ባላደራ ምናምን የሚባል ነገር የለም፤ ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባለን’ ብለው እንደነበር አስታውሰው ፣ ዶ/ር ዐቢይ ይህንን ያሉት ባላደራው ብዙ የደጋፊ መሰረት ስላለው፣ እንቅስቃሴው ሕጋዊ ስለነበረና ግፎችን የሚቃወም በመሆኑ “ባልደራስን ለማጥቃት ነው” ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ የባልደራስ አመራሮች መታሰርም መነሻው የዶ/ር ዐቢይ ንግግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት “የባልደራስን መሪዎች በማሰር፣ መግለጫ እንዳይሰጡ በማድረግ እና በማዋከብ ተጠምዶ ነበር” ያሉት አቶ ገለታው፣ “አሁንም ቢሆን የእስክንድር እና የሌሎች የባልደራስ አመራሮች እስር ፖለቲካዊ ነው” ብለው እንደሚያምኑ ተናገረዋል። እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች የባልደራስ ፓርቲ አመራሮች በቁጥጥር ስር የዋሉት የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ “በአዲስ አበባ ሁከት ለማስነሳት ሰርተዋል” በሚል ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መግለጹ ይታወሳል፡፡
የ“ተረኝነት“ ጉዳይ
አሁን ላይ በሀገሪቱ “አደገኛ የሆነ የፖለቲካ ተረኝነት እንዳለ ባልደራስ ያምናል“ ሲሉም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የቢሮ ኃላፊ ገለታው ዘለቀ ተናገረዋል።
“የብልጽግና ፓርቲ ሙሉ በሙሉ በኦህዴድ ጥላ ስር ያለ ነው“ የሚሉት ኃላፊው፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕሬዝዳንት የሚናገሯቸው ንግግሮች ለዚህ እና በሀገሪቱ ላለው “ተረኝነት“ ግልጽ ማሳያዎች እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የክልል መሪ ሆነው ሳለ “አማርኛ ቋንቋን ይህን ያህል በመቶ ደምስሰናል፤ ነፍጠኛን ሰብረናል፤ ይህንን አወዛግበናል፤ ይህንን አሳምነናል“ ማለታቸው “ተረኝነት“ ስለመኖሩ እንደሚያመለክት ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡ አቶ ሽመልስ “በርካታ ሕዝብን የሚያጋጩ ንግግሮችን እየተናገሩ አሁንም በስልጣን ላይ መሆናቸው፣ ብልጽግና ፓርቲ በኦህዴድ (በኦሮሚያ ብልጽግና) ጥላ ስር ለመሆኑ ማስረጃ ነው“ ይላሉ፡፡
አሁን ላይ “ስልጣንን እና ሀብትን ወደ አንድ ተረኛ ቡድን ለማጋባት ከፍተኛ ጥድፊያ እየተደረገ ነው“ የሚሉት አቶ ገለታው ፣ የአሰሪ እና ሰራተኛ ኤጀንሲዎች ሁኔታ እንኳን ቢታይ ቀደም ሲል “በህወሃት ሰዎች ተይዘው የነበሩት አሁን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደ ኦህደዴ (የኦሮሚያ ብልጽግና ) ዞረዋል“ ይላሉ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፣ “የአንድ ቡድን የበላይነትና ያልተገባ ጥቅም ሀገርን አንድ እርምጃ እንደማያራምድ ካለፉት 27 ዓመታት መረዳት ይቻላል” ብለዋል፡፡
ብልጽግናም ከዚህ ተምሮ “የሕወሓትን ቡድን ያፈረሰ ፓርቲ” እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡ “አሁን ላይ ተረኝነት ወይም የአንድ ቡድን የበላይነት አለ ብሎ የሚያምን ማንኛውም አካል፣ ምርመራ አድርጎ እዚህ ቦታ ይህ ነገር አለ ፤ የሚል ነገር በማምጣት በግልጽ መነጋገር ይቻላል ሲሉም ዶ/ር ቢቂላ ገልጸዋል፡፡ የተረኝነት ድርጊት አለ የሚል አካል ካለ በሰነድ የተደገፈ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚችልም ነው የተናገሩት፡፡
ዶከተር ቢቂላ አሁን ላይ “በሀገሪቱ ተረኝነት እንደሌለ” ገልጸው፣ ተረኝነት ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ወደፊት እንደማያራምዳትም አንስተዋል፡፡
የአንድ ቡድን የበላይነት የሚያቀነቅን ካለም ከዚህ በኋላ መጀመሪያ የሚታገለው የብልጽግና ፓርቲ ነው ሲሉም ነው ዶ/ር ቢቂላ የገለጹት፡፡
አዲስ አበባ እና ራስ ገዝነት
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ አዲስ አበባ ራስ ገዝ እንድትሆን ጽኑ አቋም እንዳለው የቢሮ ኃላፊው አቶ ገለታው ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው የመዲናዋን መዋቅራዊ ችግር ለመፍታት ራስ ገዝ መሆኗ ትልቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ነው የገለጹት፡፡
“የመዲናዋን መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት የሀገሪቷንም ችግር እንደመፍታት ይቆጠራል“ የሚሉት አቶ ገለታው ፣ ፓርቲያቸው አዲስ አበባ ራስ ገዝ እንድትሆን አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራ መኖሩን ከተማ አስተዳደሩ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ባለፈ የኮንዶሚኒየም ዕደላም ያለአግባብ ሲደረግ እንደነበር መንግስት ገልጿል፡፡ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች የባልደራስ አመራሮች መንግስት በመዲናዋ የተከናወኑ ዘረፋዎች መኖራቸውን ከመግለጹ አስቀድሞ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር አቶ ገለታው አስታውሰዋል፡፡