“መንግስት ካላስወጣን በስተቀር ከምርጫው አንወጣም” - መረራ ጉዲና (ፕ/ር)
መረራ “ከምንም በላይ ደግሞ ያስደነገጠን ምርጫ ቦርድ ነው” የሚሉም ሲሆን ቦርዱ ከገለልተኛነት አንጻር ጥያቄ ሊነሳባቸው የሚችሉ አካላትን በአስመራጭነት መመልመሉን ተናግረዋል
በምርጫው ለመሳተፍ ያነሳናቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉን የሚሉት መረራ ቢሮዎቻቸው መዘጋታቸውን እና አባሎቻቸው መታሰራቸውን ይገልጻሉ
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በቀጣዩ ሃገር አቀፍ ምርጫ እንደሚወዳደር አስታወቀ፡፡ ምርጫውን በተመለከተ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆታ ያደረጉት የፓርቲው ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕ/ር) በመጪው ሃገራዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡
ሆኖም በምርጫው የመወዳደራቸው ሁኔታ በመንግስት የሚወሰን ነው እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፡፡ ሊወዳደሩ የሚችሉባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችንም አስቀምጠዋል፡፡
ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ እንዲሆን “የምናነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉን” የሚሉት መረራ “መንግስት ካላስወጣን በስተቀር ከምርጫው አንወጣም” ሲሉ ይናገራሉ፡፡
መሰረታዊ የሚሏቸውን ጥያቄዎች ምንነት በተመለከተ ሲያብራሩም በሺዎች የሚቆጠሩ አባልና ደጋፊዎቻችን እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮቻችን ታስረዋል ይላሉ፡፡
በኦሮሚያ ከሚገኙ ቢሮዎቻቸው አብዛኞቹ መዘጋታቸውንም ነው የሚገልጹት፡፡
“ቢሮዎቻችን ከተዘጉ ሰዎቻችን ከታሰሩ ምን ላይ ሆነን ማንን ይዘን ነው የምንወዳደረው” ሲሉም ያጠይቃሉ፡፡
“ከምንም በላይ ደግሞ ያስደነገጠን ምርጫ ቦርድ ነው” ይላሉ ሊቀመንበሩ ቦርዱ በምርጫው ሊኖረው የሚችለውን ሚና ሲያስቀምጡ፡፡
በአስመራጭነት ሊያሰማራ በመረጣቸው ሰዎች አቅም፣ ብቃት እና ገለልተኛነት መደንገጣቸውንም ነው የሚገልጹት፡፡
ቦርዱ በአስመራጭነት የመረጣቸውን አካላት ዝርዝር ለየፓርቲው ልኳል፡፡
እኛም ተልኮልን ዝርዝሩን ተመልክተናል የሚሉት መረራ ግን በዝርዝሩ ኤሌክትሪሽያን፣ ተላላኪ፣ እንጨት አውራጅ፣ ስራ አጥ በሚል የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን መካተታቸውን ገልጸው “ኢትዮጵያውያኑን መናቄ ሳይሆን ምርጫ ለማስፈጸም መንግስትን የሚመርጥ አካል እንዴት ታሰማራለህ?” ሲሉ የምርጫውን ተዓማኒነት ተጠየቅ ውስጥ የሚከት ስራ መሰራቱን ያስቀምጣሉ፡፡
የቦርዱ ገለልተኛነት ለመረራ አይዋጥም፡፡ ዳግም እንዲዋቀር እና ከአሁን ቀደም በተቃዋሚ ጎራ ተሰልፈው ጉልህ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን ሲያደርጉ በነበሩ ሰው እንዲመራ መደረጉንም ለምርጫው ነጻና ፍትሓዊነት ዋስትና አድርጎ መውሰዱ ይቸግራቸዋል፡፡
ሆኖም ቦርዱ የምርጫ አስፈፃሚዎችን በተመለከተ ከ10 ፓርቲዎች ቀርበዋል ላላቸው ቅሬታዎች ውሳኔ መስጠቱን ከሰሞኑ በማህበራዊ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በመግለጫው ያለምንም ማስረጃ የቀረቡትን አቤቱታዎች አለመቀበሉን ያስታወቀ ሲሆን የፓርቲ አባልነት መክፈላቸውን የሚያመለክት ማስረጃ የቀረበባቸውን ተመልማዮች ከአስፈጻሚነት መሰረዙን ገልጿል፡፡
ስራ ፈጠራ ኮሚሽንን እና ማእከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣንን በመሳሰሉ የመንግስት ተቋማት በኩል የሚመለመሉ ሰዎች መካተት የለባቸውም የሚለውን ቅሬታ አለመቀበሉን የማይታወቁ ናቸው የተባሉ አስፈፃሚዎች አድራሻ እንዲጣራ ስለማዘዙም ነው በመግለጫው ያስታወቀው።
የቦርዱ በገለልተኛነት ዳግም መደራጀት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ሳይቀር ይሁኝታ እና አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኘ በመጥቀስ ለምን እርሳቸውና ፓርቲያቸው በቦርዱ ላይ አመኔታ ሊያጡ እንደቻሉ አል ዐይን የጠየቃቸው መረራ “ሰብሳቢዋ ቦርዱን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመረጡበት እለት ጭምር ልዩነት እንደነበረኝ ተናግሬያለሁ” ሲሉ መልሰዋል፡፡
ምርጫው “በእኛ ግምት እና እይታ በኢትዮጵያ ሶስት ነገሮችን ካላመጣ ምንም ትርጉም የለውም” ሲሉም ይናገራሉ አንጋፋው ፖለቲከኛ፡፡
ዘላቂ ሰላም ሊመጣ፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከምርጫው ልትወለድ እና ብልጽግና ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ ሊመጣ እንደሚገባ በመጠቆም፡፡
ኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበሩን አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮቹ እና ጃዋር መሃመድን የመሳሰሉ አባላቱ ታስረውበታል፡፡
የታሰሩት ከሰኔ 22ቱ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በተለይም ግድያውን ተከትለው በዋናነት በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ ካጋጠሙ ከፍተኛ የጸጥታ ችግሮች ግድያ እና የንብረት ውድመት ጋር በተያያዘ ክሶች ተመስርተውባቸዋል፡፡
በርሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ መገለጹም የሚታወስ ነው፡፡