ኢትዮጵያ ለሁለት አዳዲስ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት ያወጣችው ዓለም አቀፍ ጨረታ ተዘጋ
በኢትዮጵያ እስካሁን ብቸኛው የቴሌኮሙኒኬሽን ፍቃድ ያለው ኢትዮ ቴሌኮም ነው
በጨረታው ለመሳተፍ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነድ አስገብተዋል
ኢትዮጵያ ለሁለት አዲስ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ፈቃዶች ላወጣችው ጨረታ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች ሰነድ አስገቡ።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ለሁለት አዲስ የቴሌኮሙኒኬሽን ፈቃዶች የወጣው ጨረታ በዛሬው እለት መዘጋቱንም የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዛሬው እለት በተካሄደው የጨረታ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ በጨረታው ላይ ለመሳተፍ ሰነድ ያስገቡ ኩባንያዎች ስም ዝርዝር ይፋ ተደርጓል።
በዚህም ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ በተባለ ተቋም ስም ሳፋሪኮም ከኬንያ፣ ቮዳፎን ከብሪታኒያ፣ ቮዳኮም ከከደቡብ አፍሪካ፣ ሲ.ዲ.ሲ ግሩፕ ከብሪታኒያ እና ሰሚቶሞ ኮርፖሬሽን ከጃፓን በጥምረት እንዲሁም ኤ.ቲ.ኤን ከደቡብ አፍሪካ ሰነድ አስገብተዋል።
የሚሰጡት ሁለት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ፈቃዶች አሸናፊዎች ባለሥልጣኑ በተረከባቸው የጨረታ ሰነዶች ላይ የሚያከናውነውን የቴክኒክ እና የፋይናንስ ግምገማዎች ካጠናቀቀ በኋላ የሚገለፅ መሆኑም ታውቋል።
ባለሥልጣኑ ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ ለሁለት ኩባንያዎች የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የፍላጎት መግለጫ መጠየቂያ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ አይዘነጋም።
ሂደቱ መንግስት የገጠመውን የውጭ መንዛሬ ዕጥረት ለመፍታት እና ውድድርን ለመፍጠር ካቀዳቸው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎች አንዱ መሆኑንም ጠቅሷል።