በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡ አገደ
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡ አገደ
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከመጋቢት 14/2012 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ተማሪ ለማንኛውም አይነት አገልግሎት ከግቢ መውጣትም ሆነ መግባት እንደማይችል አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ተማሪዎችና ሰራተኞች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎች መመገቢያ ስርዓት ውጭ (የነን ካፌ ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎች) በግቢ ውስጥ ባሉት ሶስት የተማሪ ካፊቴሪያዎች እንዲመገቡ እንዲሁም ከአሁን በፊት ከግቢው ለተግባር ልምምድ የወጡ ተማሪዎች በተመደቡበት ቦታ እየሰሩ እንዲጠብቁ መመሪያ አስተላልፏል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ቤተሰብ የሄዱ ተማሪዎች ወደ ግቢ መግባት እንደማይችሉና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ጥንቃቄ እያደረጉ እንዲቆዩም ነው ዩኒቨርሲቲው ያሳሰበው፡፡
ተማሪዎች ወደ ዋናው ምግብ ቤት ሲገቡም ሆነ ሲመገቡም ሳይተፋፈጉ (በቡድን ሳይሆኑ በተናጠል) ተገቢውን ርቀት ጠብቀው እንዲስተናገዱ ያሳሰበው ዩኒቨርሲቲው የመመገቢያ ሰዓት ፕሮግራም በየኮሌጆቻቸው ሊወጣ የሚችል መሆኑን፣ የጋራ መጠቀሚያ በሆኑት ፑል ቤቶች፣ ኳስ መመልከቻ ቦታዎች ፣ካፍቴሪያዎች ላይ በቡድን ሆኖ መቀመጥና መጠቀም የማይቻል መሆኑን፣ የተማሪዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል ሁሉም መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች መግባት እንደማይችሉ አስታውቋል፡፡
ነገር ግን ለስራው የሚያስፈልጉ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡