የክርስቶስ ልደት የሚከበርበት የልደት በዓል በመጣ ቁጥር የገና ጨዋታዎችን መጫወት በኢትዮጵያ በተለይ ቀደም ባሉት ጊዜያት የተለመደ ነው
የገና ጨዋታ መቼ እንደተጀመረ የሚገልፅ መረጃ ባይኖርም ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት እንደነበር ይነገራል።
አርሶ አደሮች በመኸር ወቅት ሰብላቸውን ከሰበሰቡ በኋላ ከብቶቻቸውን እያገዱ በሜዳማ ስፍራዎች የሚጫወቱት ጨዋታ ነውም ይባላል የገና ጨዋታ፡፡
በገና ጨዋታ ጨዋታ ወቅት ግጥሞችን መደርደር መዝፈን መጫወቱ የተለመደ ነው፡፡ “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ፤ በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ” እየተባለ ይገጠም እንደነበርም ይነገራል፡፡
ገና ጨዋታ የራሱ ሃይማኖታዊ አንድምታዎች አሉት፡፡ በተለይ በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ዘንድ የሚሰጠው የራሱ ሃይማኖታዊ አንድምታ አለ፡፡ ከሀይማኖታዊ እሴቶቹ ባሻገር የማህበረሰቡ ባህላዊ እሴቶችና ሌሎች ገጽታዎች የሚንጸባረቁበት ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ አንስቶ ደግሞ የራሱ የጨዋታ ህግ ወጥቶለት ጨዋታው በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
12ኛው የአዲስ አበባ የባህል ስፖርት ውድድር ከሰሞኑ በጃንሜዳ በተካሄደበት ወቅት የስፖርት ጋዜጠኞች ከአርቲስቶች ተጫውተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ፌደሬሽን በ2006 ዓ.ም በገና ጨዋታ ዙሪያ ባካሄደው ጥናት ጨዋታው ከሰባት በላይ የጨዋታ ህጎች አሉት፡፡
ነዋሪነቱ በአዲስ በአዲስ አበባ የሆነው አቶ ፍቃዱ ለማ ከዚህ በፊት የገና ጨዋታ ተጫዋች ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የሚካሄዱ የገና ጨዋታቸዎችን እንደሚዳኝ ይናገራል።
አንድ የገና ጨዋታን ለማካሄድ በሁለት የ30 ደቂቃ አጋማሾች የተከፈለ እና የ15 ደቂቃ እረፍት ያለው 60 ደቂቃ ያስፈልጋል።
ተጋጣሚዎች አቻ ከሆኑ የሚዳኙበት ህግ አለው። ተጨማሪ 15 ደቂቃ ተሰጥቶ አሸናፊው እንዲለይ ይደረጋል እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ።
የጨዋታው ተጋጣሚ ሁለት ቡድኖች እያንዳንዳቸው 1 በረኛ እና 9 ተጨዋቾች በድምሩ 10 ተጫዋቾች ሲኖራቸው ተጋጣሚ ቡድኖች እያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት ተጫዋቾችን መቀየር ይችላሉ፡፡
የገና ጨዋታ መጫወቻ ሜዳ ስፋቱ 80 በ40 በሆነ ሜዳ እንዲሁም የጎሎቹ ስፋት ደግሞ 1 ሜትር ከ20 ሴንቲ ሜትር በአንድ ሜትር መሆኑን ባለሙያው ይገልጻል፡፡
የገና ጨዋታ ወቅታዊ እና አገር በቀል የባህላዊ ጨዋታ ነው የሚለው ፈቃዱ ስፖርቱ በትምህር ስርዓቱ ውስጥ ተካቶ ትውልዱ እንዲያውቀው ቢደረግ ጥሩ ነው ሲል ይመክራል፡፡
ጨዋታው ወይም ውድድሩ የሚካሄድበት የራሱ ሜዳ የለውም፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ስፖርቱ ወቅታዊ እና የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚጫወቱት እንዲሆን አድርጎታል የሚሉት አቶ ፈቃዱ መንግስት ይህ ውድድር እንዲሰፋ እና ትውልዱም እንዲያውቀው ቢያደርግ እንደሚበጅ ገልጿል፡፡
አንድን ስፖርት ተወዳጅ እና እያደገ እንዲሄድ የሚያደርገው የጨዋታ ህግ እና በቂ ውድድሮች ሲካሄዱ በመሆኑ በቂ ውድድሮች እንዲፈጠሩም ባለሙያው ጠይቋል፡፡