ኪነ ህንጻዊ ይዘቱን የሚያጎሉ በርካታ ቅርጻ ቅርጾችን የያዘውን ጥንታዊ ካቴድራል ለማደስ የሚያስችለው ጥናት ተጠናቋል ተብሏል
መሃል አራት ኪሎ ቤተ መንግስት አቅራቢያ የሚገኘው እድሜ ጠገቡ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ሊታደስ ነው፡፡
ካቴድራሉን ለማደስ ላለፉት 9 ያህል ወራት ሲካሄድ የነበረው ዝርዝር ጥናት ተጠናቋል ተብሏል፡፡
ጥናቱ በካቴድራሉ ህንጻ አሰሪ ኮሚቴ አስተባባሪነት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ፈቃድና ክትትል በተቋራጮች የተካሄደ ሲሆን እድሳቱን ለማካሄድ በሚያስችል መልኩ መካሄዱ ተነግሯል፡፡
የጥናቱን መጠናቀቅ በማስመልከት ህንጻ አሰሪ ኮሚቴው ዛሬ ረፋድ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫው ካቴድራሉ ሳይጠገን ለረዥም ዓመታት በማገልገሉ ምክንያት ውስጣዊ እና ውጫዊ ክፍሎቹ ማርጀታቸው፣ ማፍሰስ እና የተለያዩ አካላዊ ጉዳቶችን ማስተናገድ መጀመራቸው ተነግሯል፡፡
ከከፍተኛ የውሃ ስርገት ስጋት ባሻገር ጣራው እያፈሰሰ፣ ግድግዳው እየተቀረፈ እና ሞዛይኮቹ እየረገፈ በመውደቅ እንደተጎዳ በጥናቱ ተለይቷልም ነው የተባለው፡፡
በመሆኑም ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አገልግሎቱ ባሻገር ትልቅ ሃገራዊ አበርክቶ ያለውን ካቴድራሉን እና ቅርጻቅርጾቹን ኪነ ጥበባዊና ቅርሳዊ ይዞታቸውን በጠበቀ መልኩ ለመጠገንና ለማደስ ዝግጅቶች በመደረግ ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ እድሳቱ የካቴድራሉን ቅጥረ ግቢ እንደሚያካትትም ነው የተገለጸው፡፡
እድሳቱ ሁለት ገደማ ዓመታትን ሊፈጅ ይችላልም ነው የተባለው፡፡ ከ80 እስከ 100 ሚሊዮን ብር ሊወስድ እንደሚችል የተገመተም ሲሆን መጠነኛ እድሳቶች እየተደረጉለት ቀጣዮቹን 50 ዓመታት እንዲያገልግል ሆኖ ይታደሳልም ነው የተባለው፡፡
ስራውን በቶሎ ለመጀመር በመጪው ጥር 7 ቀን 2014 ዓ/ም ታቦተ ህጉ ከካቴድራሉ ወጥቶ ወደ በዓለወልድ ቤተክርስያን እንደሚዛወርም ነው የተገለጸው፡፡
እድሳቱን የሚያከናውኑ ብቁ ተቋራጮችን ለመለየት የሚያስችለው ዝርዝር መስፈርት ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን መላኩም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
ጥንታዊው “የፓን አፍሪካኒዝም የጥበብ ት/ቤት በኢትዮጵያ”- አለፈለገ ሰላም
“ትልቅ ሃገራዊ ቅርስ” ሲሉ ካቴድራሉን የገለጹት የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ/ር) እሴቱን ጠብቆ እንዲታደስ ሙያዊ እገዛና ክትትሎችን እናደርጋለን ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
የጨረታውን ሂደት እና የተጫራቾችን አቅም ለመመዘን እገዛዎችን እንደሚያደርጉም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
የአጼ ኃይለ ስላሴን የንግስና በዓለ ሲመት ያስተናገደው ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የመሪዎች፣ የጀግኖች አርበኞች እና የታዋቂ ሰዎች ዘላቂ የማረፊያ ስፍራ ነው፡፡ በብዙዎች ይጎበኛልም፡፡
የካቴድራሉ ግንባታ በ1922 ዓ/ም የተጀመረ ሲሆን በፋሽስት ጣሊያን ወረራና በተለያዩ ምክንያቶች ተጓቶ በ1936 ዓ/ም መጠናቀቁን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡