ዶ/ር አረጋ ይርዳው ከተለያዩ አካላት የሚደርስባቸው ጫና ለስራቸው መልቀቅ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል
ዶ/ር አረጋ ይርዳው ከተለያዩ አካላት የሚደርስባቸው ጫና ለስራቸው መልቀቅ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል
ዶ/ር አረጋ ይርዳው የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለሚድሮክ ኢንቨስትመንት ባለሀብት እና ሊቀመንበር ክቡር ዶ/ር ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ማስገባታቸው በድርጅቱ ማህበራዊ ሚዲያ ተገልጿል፡፡
ከተለያዩ አካላት የሚደርስባቸው ጫና በስራቸው ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑ ለስራቸው መልቀቅ ምክንያት እንደሆነ ዶ/ር አረጋ በጻፉት ደብዳቤ ላይ አብራርተዋል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ ከሁዳ ሪል እስቴት ኩባንያ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሪል እስቴቱ ከራሱ ሰራተኞች ውጭ በሆኑ ግለሰቦች አማካኝነት በተከታታይ ስራቸው እንዲታወክ ማድረጉን እና ለዚህም መፍትሔ እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄ መፍትሄ አለማግኘቱን ገልጸዋል፡፡
በሁለተኛነት ከሚድሮክ ወርቅ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ተግዳሮት እንደሆነባቸው ነው ያብራሩት፡፡
ሶስተኛው ከኤልፎራ ኩባንያ ጋር በተያያዘ ስራ አጥ ወጣቶች የሚያቀርቡት የመሬት ስጡን ጥያቄ የኩባንያውን የግብርና ስራ ሲያስተጓጉል መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ ጥያቄው በእርሳቸው ሊመለስ እንደማይችል በመጥቀስ፣ የመሬት ጥያቄው በመንግስት በኩል ለሚድሮክ ሊቀመንበር እና ባለሀብት ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ እንዲቀርብ ቢደረግም ተቀባይነት አለማግኘቱን ዶ/ር አረጋ የጻፉት ደብዳቤ ያሳያል፡፡ ይህ ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ ለወደፊት በሚሰሩ ስራዎችም ላይ ተጽእኖው የጎላ በመሆኑ ራሳቸውን ማግለል እንደመረጡ ዶ/ር አረጋ ይፋ አድርገዋል፡፡
ይሁንና የ25 ኩባንያዎች የዋና ስራ አስፈጻሚነት ኃላፊነታቸውን በመተው ከተፈቀደላቸው የ26ኛው ተቋም ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነው መቀጠል እንደሚፈልጉም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች መስኮች ሀገራቸውን ማገልገላቸውን እንደሚቀጥሉም ዶ/ር አረጋ ጠቅሰዋል፡፡
ዶ/ር አረጋ ይርዳው በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ባለሀብት እና ሊቀመንበር ክቡር ዶ/ር ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ጥያቄ ከዛሬ 22 ዓመታት በፊት ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ፣ ከተመለሱበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ዛሬ ከሰዓት በኋላ ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ዶ/ር አረጋ ይርዳውን ከኃላፊነት አንስተው በምትካቸው አቶ ጌታቸው ሐጎስን የሚድሮክ ጊዜያዊ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርገው ሰይመዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ሐጎስ
በሚድሮክ ባለቤትና ሊቀመንበር ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የተፈረመው ደብዳቤ፣ ለቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚና ለጊዜያዊ ሃላፊው መድረሱን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ከ20 ዓመታት በላይ ሚድሮክን የመሩት ዶ/ር አረጋ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዚዳንት ሆነው እንደሚቀጥሉም ሊቀመንበሩ የጻፉት ደብዳቤ ያመለክታል፡፡
አዲሱ ጊዜያዊ የሥራ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሐጎስ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ውስጥ ሲሰሩ የቆዩ እንደሆኑም ነው ያገኘነው መረጃ የሚያሳየው፡፡