መንግሥት የ2017 በጀት ለመሸፈን ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮች ፣ከውጭ ዕርዳታ እና ብድር 612.7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል
የኢትዮጵያ መንግሥት ለ2017 ያቀረበው 971.2 ቢሊዮን ብር በጀት በሙሉ ድምጽ ጸደቀ፡፡
ለሚቀጥለው ዓመት ጥቅም ላይ እንዲውል በምክር ቤቱ የጸደቀው በጀት ከዘንድሮው በ169.56 ቢሊዮን ብር ይበልጣል።
በ2017 የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን 2.5 በመቶ ድርሻ የሚኖረው ሲሆን በጀቱ የ358.5 ቢሊዮን ብር ጉድለት አለበት፡፡
ከ2017 በጀት 451 ቢሊዮን ብር የተመደበው ለመደበኛ ወጪ ነው። ለካፒታል በጀት 283.2 ቢሊዮን ብር፣ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ 222.7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 140 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።
በካፒታል ወጪ መንገድ፣ ትምህርት፣ መከላከያ፣ ጤና እንዲሁም ፍትህ እና ደሕንነት በፌዴራል የመደበኛ እና ካፒታል ወጪ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የተሰጣቸው ናቸው።
ከ2017 በጀት 139.3 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ የመደበው መንግስት በበጀት አመቱ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የዕዳ ክፍያ አንዱ ነው ብሏል፡፡
ለመደበኛ ወጪ የተደለደለው በጀት ለዕዳ ክፍያ የተያዘው ብር 139.3 ቢሊዮን ሲሆን ይህም ለመደበኛ ከተመደበው ጠቅላላ ወጪ ውስጥ የ30.9 በመቶ ድርሻ ይዟል
ለዕዳ ክፍያ ከተያዘው በጀት ውስጥ 54.8 በመቶው ለሀገር ውስጥ ዕዳ ክፍያ እንዲሁም ቀሪው 45.2 በመቶው ለውጭ ሀገር ዕዳ ክፍያ የሚውል ነው።
መንግሥት የ2017 በጀት ለመሸፈን ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮች፤ ከውጭ ዕርዳታ እና ብድር 612.7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል።
ከዚህ ውስጥ 563.6 ቢሊዮን ብር ከሀገር ውስጥ ገቢ፤ 7.3 ቢሊዮን ብር በቀጥታ በጀት ድጋፍ ከሚገኝ ከመሠረታዊ አገልግሎት ዕርዳታ እንዲሁም 41.8 ቢሊዮን ብር ከፕሮጀክቶች ዕርዳታ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ መንግስት ለፓርላማው ያቀረበው የበጀት ጥያቄ ላይ ተመላክቷል፡፡
በዚህም መሠረት የሚቀጥለው ዓመት በጀት 358.5 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንደሚገጥመው ተጠቅሷል።
የበጀት ጉድለቱ ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን (GDP) ያለው ድርሻ 2.5 በመቶ ይሆናል።
መንግስት በሚቀጥለው ዓመት በጀት የሚገጥመውን ጉድለት ለመሙላት ከሀገር ውስጥ 325.6 ቢሊዮን ብር የመበደር ዕቅድ አለው።
ባለፉት አመታት 30 በመቶ እና ከዛ በላይ የነበረውን የዋጋ ግሽበት ወደ 23 በመቶ ዝቅ አድርጊያለሁ የሚለው መንግሰት በሚቀጥለው ዓመት ወደ 12 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እስራለሁ ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ በሰጡበት ወቅት የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ከ6 አመት በፊት ከነበረበት 86 ቢሊየን ዶላር ወደ 205 ቢሊየን ዶላር ከፍ ማለቱን ተናግረው ፤ዘንድሮ በኢኮኖሚ 7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡