ጠ/ሚ አብይ የጸጥታ ሃይሎች ስለሚቀርብባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰት ምን ምላሽ ሰጡ?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ እንደራሴዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፥ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተቋም “ለቀጠሩት ሃይሎች ሪፖርት የሚያቀርብ” ነው ሲሉ ከሰዋል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን በተደጋጋሚ ባወጣቸው ሪፖርቶች ማመላከቱ ይታወሳል
የሰብአዊ መብት ጉዳይ ከዋናው ትርጉሙ እየወጣ ፖለቲካዊ መጠቀሚያ ሆኗል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው ይህን ያሉት።
ከምክርቤት አባል በአማራ ክልል የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች “የጅምላ ግድያ እየፈጸሙ ነው፤ የሲቪል ተቋማት እየወደሙ ነው፤ ፖለቲከኞች በማንነታቸው ብቻ ለጅምላ እስር ተዳርገዋል” የሚል ጥያቄ ቀርቧል።
አለማቀፍ ተቋማትም በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት በአለማቀፍ ገለልተኛ ተቋም እንዲመረመር ተጠይቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በምላሻቸው፥ “የሰብአዊ መብት ጉዳይ ከዋናው ትርጉሙ እየወጣ ፖለቲካዊ መጠቀሚያ ሆኗል፤ ብዙ የአፍሪካ ሀገራትም የሚታመሱት በዚሁ ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስም በይፋ ባይጠቅሱትም በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀስውን የሰብአዊ መብት ተቋም (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን) “በቀጣሪዎቹ” ተጽዕኖ ስር ወድቋል ነው ያሉት።
“እኛ ደመወዝ ለማንከፍለው፤ ሌሎች ሃይሎች ለቀጠሩት (ተቋም) ለሌሎች ሪፖርት እንዲያደርግ” መፍቀድ ዋጋ ያስከፍላል ሲሉም ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን በተደጋጋሚ ባወጣቸው ሪፖርቶች ማመላከቱ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም በሀገሪቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ባመኑበት ንግግራቸው፥ “ለስህተቶቹ ሃላፊነት መውሰድ አለብን” ያሉ ሲሆን፥ በሺዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በወታደራዊ ፍርድቤቶች ጥፋተኛ ተብለው በእስር ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የጅምላ ግድያ ላይ ተሳትፈዋል በሚል የሚቀርበው ወቀሳ ግን መሰረተ ቢስ መሆኑን ነው የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ለሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሃይሎች የንግግር ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስት ለሰላም ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን በመጥቀስም ከሰላማዊ መንገድ ውጭ በምርጫ የተመረጠን መንግስት በሃይል ለማንሳት የሚደረግ ሙከራ እንደማይሳካ ጠቁመዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሰሜኑን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸምን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በራያና ጸለምት ተፈናቃዮችን መመለስ መጀመሩን ተናግረዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመር እና የሽግግር መንግስት ማቋቋም ዋነኛ ጉዳዮች እንደነበሩ በማንሳትም፥ በስምምነቱ “የተፈናቀሉ ሰዎች እና የአከራካሪ ወሰን ጉዳይ በህገመንግስቱ ይመለስ የሚለው ሀረግ በዝርዝር እቅዳችን እንጂ በፕሪቶሪያው ስምምነት የለም” ብለዋል።
በራያ የተካሄደው የተፈናቃዮች ማስመለስ ሂደት ከተቀመጠው አቅጣጫ ውጪ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “እልኸኝነታቸው ያልቀነሰና የበዛ ቁጣ ያላቸው” ያሏቸው አካላት ተፈናቃዮችን የማስመለሱን ሂደት እያደናቀፉ መሆኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የህወሃት ዋናዋና አመራሮች ተፈናቃዮችን የማስመለሱ ሂደትና አወዛጋቢ የወሰን ጉዳዮች በሰላማዊና በህገመንግስታዊ አካሄድ እንዲፈታ ይፈልጋሉ ብለው እንደሚያምኑም በማከል።
ተፈናቃዮችን የመመለሱ ስራ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ይቀጥላልም ብለዋል።
ሱዳን እና ሶማሊያ
በሱዳን ጦርነት እና ከሶማሊያ ጋር ለወራት በዘለቀው ሰጣ ገባም ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
“"የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሊያ ጋር ጸብ የለውም፤ የሶማሊያ መንግስት ግን ኢትዮጵያን ከማናገር ይልቅ በየሰፈሩ እየዞረ መክሰስን መርጧል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ አንድነት ጥያቄ እንደሌላትና ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ዋነኛ ጥያቄ ወደብ መሆኑንና ለሌሎች ጎረቤቶቿ ያቀረበችው ጥያቄ ምላሽ ሲያጣ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟንም አውስተዋል።
ኢትዮጵያ “ሶማሊያ እንድጎዳ እንድትፈራርስ አትፈልግም፤ እንደዛ ቢሆን ልጆቿን ወደ ሶማሊያ አትልክም ነበር” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ ከመካሰስ ይቅል ልዩነትን በንግግር መፍታት እንደሚሻል አብራርተዋል።
ሱዳንን በተመለከተም ኢትዮጵያ ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ገለልተኛ አቋም በመያዝ ጦርነቱ እንዲቆም ጥረት ማድረጓን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወሱት።
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በሱዳን የተያዙ የኢትዮጵያ መሬቶችን በስአታት ውስጥ ማስመለስ የሚቻል ቢሆንም የሱዳን መረጋጋትን እየጠበቅን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሱዳን ያለችበትን ሁኔታ መጠቀሚያ ማድረግ አልፈለግንም ብለዋል።
ካርቱም ከሁለት አመት በላይ የኤሌክትሪክ ውዝፍ ክፍያ ቢኖርባትም ኤሌክትሪክ አላቋረጥንም ሲሉም ተናግረዋል።