የሱዳን ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? ስለጦርነቱ ምን ማወቅ ይፈልጋሉ?
በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ኃሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ስድስተኛ ቀኑን ይዟል
ተዋጊዎች የእርዳታ ሰራተኞችን፣ ሆስፒታሎችንና ዲፕሎማቶችን ኢላማ ማድረጋቸው ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን አስጨንቋል
በሱዳን ካርቱም ወታደራዊ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ውጥረት ነግሷል።
የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊቱ ያወጁት የ24 ሰዓት ተኩስ አቁም መክሸፉን ተከትሎ ሱዳንን ለመቆጣጠር ጦርነቱ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል።
የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ቅዳሜ እለት በሱዳን ጦር ኃይሎችእና በፈጥኖ ደራሽ ሰራዊቱ (አርኤስኤፍ) መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ካርቱም፣ አጎራባች በሆነችው ኦምዱርማን እና በሌሎችም አካባቢዎች ከባድ ውጊያ አለ።
የዓለም ጤና ድርጅት የሱዳን ጤና ጥበቃ ሚንስቴርን ጠቅሶ እንዳለው በግጭቱ ቢያንስ 270 ሰዎች ሲገደሉ፤ ከ2 ሽህ 600 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ሲል አርቲ ዘግቧል።
የሱዳን ዶክተሮች ህብረት በዋና ከተማዋ እና በአጎራባች ከተሞች ከሚገኙት ሆስፒታሎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ህሙማንን ማገልገል ሲሳናቸው፤ የተወሰኑት ደግሞ በቦምብ ከተመቱ በኋላ ጥቃት እና ዝርፊያ ደርሶባቸዋል።
የግጭቱ መንስኤ ምንድን ነው?
ግጭቱ እየተቀጣጠለ ያለው የጦሩ መሪ በሆኑት በጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን እና በተቀናቃኛቸው በጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የስልጣን ሽኩቻ ነው።
ውጥረቱ የተፈጠረው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ወደ ሀገሪቱ ጦር ኃይል ለማዋኻድ እና ይህን አሰራር ለመቆጣጠር የስልጣን ወሰን ላይ ነው።
የውህደቱ ሂደት በሱዳን የሽግግር ስምምነት ላይ የተገለጸ ወሳኝ መስፈርት ነው። እሱም በመጀመሪያ በፈረንጆች ሚያዝያ አንድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም እስካሁን አልተፈረመም።
የሽግግር ስምምነቱ ምንድን ነው?
እ.ኤ.አ ሚያዚያ 2019 በሁለቱ ወገኖች በጋራ የተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት፤ ለ30 ዓመታት በስልጣን ላይ የነበሩትን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽርን ከስልጣን እንዲወርዱ አድርጓል።
በነሀሴ 2019 በሽግግር ወታደራዊ ም/ቤት እና የነጻነትና የለውጥ ህብረት መካከል 11 አባላት ያሉት የሽግግር ሉዓላዊነት ም/ቤት በማቋቋም በሲቪል የሚመራ የሽግግር መንግስት እንዲፈጠር መንገዱን የሚጠርግ የስልጣን መጋራት ስምምነት ተደረሰ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቱ የምትመራው በሉዓላዊ ም/ቤቱ ሲሆን የሰራዊቱ አዛዥ አል-ቡርሃን በፕሬዝዳንትነት እና ፈጥኖ ደራሽ አዛዡ ሄሚቲ ምክትል ሆነው አገልግለዋል።
በጥቅምት 2021 ሌላ መፈንቅለ መንግስት የሽግግር ስምምነቱን በማስተጓጎሉ ባለፈው ታህሳስ ወር አዲስ ስምምነት ላይ ተደረሰ።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለምን ከሀገሪቱ ጦር ኃይሎች ጋር መቀላቀልን ይቃወማል?
በሄሚቲ እና በአል-ቡርሃን መካከል የጦሩ ዋና አዛዥን በመሾም ላይ አለመግባባት እንደነበር ሪፖርቶች ቀርበዋል። ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊቱ ቦታውን የሲቪል ርዕሰ መስተዳድር እንዲይዝ ይደግፋል የተባለ ሲሆን፤ ይህን ደግሞ ጦሩ ይቃወማል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ "በጦር ኃይሉ ውስጥ መቀላቀልን ስልጣኔን አጣለሁ” በሚል ስጋት እንደሚቃወም ውስጥ አዋቂዎች ተናግረዋል።
ግጭቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብን እንዴት ነካው?
ተዋጊዎች የእርዳታ ሰራተኞችን፣ሆስፒታሎችን እና ዲፕሎማቶችን ኢላማ አድርገዋል ተብሏል። የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል በሱዳን የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር "በራሳቸው መኖሪያ ቤት ጥቃት ደርሶባቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ ተሽከርካሪዎች ኮንቮይ በተመሳሳይ ቀን ጥቃት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
የህንድ ኤምባሲም እለት ከዜጎቹ አንዱ በጥይት ተመቶ መሞቱን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሦስት ሰራተኞች ከተገደሉ በኋላ ድርጅቱ በሱዳን የሚያደርገውን ስራ ለጊዜው አቁሟል።
መውጫ ቀዳዳው ምንድን ነው?
ሱዳናዊያን እፎይታ እና አቅርቦቶችን እንዲያገኙ ተፋላሚዎቹ ግጭቱን እንዲያቆሙ ግፊት እየተደረገ ነው። ሁለቱም ወገኖች ደርሰውት የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ እርስ በእርስ ሲሉ ተከሰዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ውስጥ “ሙሉ በሙሉ የተኩስ አቁም ለማድረግ ሙሉ ቁርጠኝነት አለኝ” ሲለሰ ትናንት ረቡዕ አሳውቋል።