ዐቢይ አህመድ የኢጋድን ‘የእናሸማግላችሁ’ ጥያቄ ሳይቀበሉ ቀሩ
ጉዳዩ ዓለም አቀፋዊ መልክ ሊይዝ የማይገባው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ነው ስለማለታቸውም ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ለ4 ያህል ጊዜያት ያቀረቡላቸውን ጥሪ ሳይቀበሉ ቀርተዋል ተብሏል
ዐቢይ አህመድ የኢጋድን ‘የእናሸማግላችሁ’ ጥያቄ ሳይቀበሉ ቀሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የቀረበውን የሽምግልና ጥሪ ሳይቀበሉ ቀሩ፡፡
የቀጣናዊው ተቋም መሪ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በ4 የተለያዩ ጊዜያት ስልክ በመደወል የኢትዮጵያ አቻቸውን ለማግባባት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ሱዳን ትሪቢውን የሃምዶክን ቢሮ አጣቅሶ የዘገበውን ሂቃያት ጋዜጣን ዋቢ አድርጎ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው ዘገባ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉዳዩ ዓለም አቀፋዊ መልክ ሊይዝ የማይገባው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ሃምዶክ ባለፈው ዓመት የኢጋድ ሊቀመንበር ሆነው ዐቢይ አህመድን መተካታቸው ይታወሳል፡፡
“የህወሀት ጁንታ ቡድን ትላንት የቀረቡለትን የድርድር እና የውይይት እድሎች ሁሉ አምክኖ ግብአተ መሬቱ ሊፈጸም ሲቃረብ የአደራዳሪ ያለ ብሎ መጮህ ጀምሯል” ሲል መግለጫ ያወጣው ብልጽግና ፓርቲ “አሁን ሰአቱ የድርድር ሳይሆን የፍርድ ሆኗል” ብሏል፡፡
“ትዕግስት ሊቀይረው ያልቻለው ጁንታ”ያለውን ህወሓትን “በህግ አግባብ ተጠያቂ ማድረግ ግዴታ የሆነበት ሰአት ላይ” እንደደረሰም ነው የገለጸው፡፡
“የተጀመረው ጉዞ ጦርነት ሳይሆን የህግ ማስከበር ስርአት ነው” ያለም ሲሆን “በአጭር ጊዜ ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ በማቅረብ” እንደሚጠናቀቅም አስታውቋል፡፡
ብልጽግና ህወሓት ድርድን እናስቀድም የማለቱ ዋና ዓላማ “ሰላምን ማውረድ ሳይሆን በድርድር ምክንያት ጊዜን መግዛት ነው” ሲል ትናንት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
“ኢትዮጵያ ወደ ትርምስ ትገባለች የሚለው ስጋት የሃገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት ካለመረዳት የመነጨ ነው” ሲሉ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “አሁን እየተካሄደ ያለው ህግ የማስከበር ስራ ሰላምንና መረጋጋትን በማስፈን ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ያለመ ነው ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል” ሲሉ መልዕክት ማስፈራቸውም አይዘነጋም፡፡