ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ስለ ሕዳሴው ግድብ ለዲአር ኮንጎ ገለጻ እንደሚያደርጉ ተጠቆመ
በቀጣዩ ወር የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የምትሆነው ኮንጎ በግድቡ ዙሪያ ከግብፅ ጎን ስለመሆኗ ይነገራል
ፕሬዝዳንቷ ለስራ ጉብኝት ዛሬ ወደ ዲአር ኮንጎ አቅንተዋል
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በኮንጎ ቆይታቸው በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዲአር ኮንጎ በቀጣዩ ወር የካቲት 2021 ፣ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን ትረከባለች፡፡ ግብፅ ከሀገሪቱ ጋር ያላትን ወዳጅነት ታሳቢ በማድረግ ፣ በወቅቱ የሕብረቱ ሊቀመንበር በደቡብ አፍሪካ መሪነት የሚደረገው የሕዳሴ ግድብ ድርድር ወደ ዲአርሲ አደራዳሪነት እንዲሸጋገር ፍላጎት እንዳላት ይገለጻል፡፡ ግብፅ እና ሱዳን የደቡብ አፍሪካ የሊቀ መንበርነት ጊዜ እስኪያበቃ ድርድሩ እንዲዘገይ ፍላጎት እንዳላቸው ከሁለት ሳምንታት በፊት የገለጹት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “ካርቱምና ካይሮ ድርድሩን አሰልቺ አንዲሆንም አድርገዋል” ብለዋል፡፡
ሀገራቱ የሕዳሴ ግድብ ድርድር “በጥቅሉ በአፍሪካ ሕብረት ፣ በተናጠል ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ሊቀመንበርነት መፍትሄ እንዲያገኝ ፍላጎታቸው አይደለም” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የዲአር ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፍሊክስ ቺሲኬዲ ከሳምንታት በፊት ለግብፅ አቻቸው በአማካሪያቸው በኩል በላኩት መልዕክት በሕዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ሀገራቸው “ከግብጽ ጎን እንደምትቆም” ማረጋገጣቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ካላቸው ቅርርብ የተነሳ ፣ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚደረገው ድርደር ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኮንጎ የመዛወሩን ጉዳይ ግብፅ አጥብቃ ትፈልገዋለች ነው የተባለው፡፡
በዛሬው ዕለት ወደ ዲአር ኮንጎ ያመሩት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ፣ የጉብኝታቸው ዋና ዓላማ የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ ለሀገሪቱ መሪ ለማስረዳት መሆኑን አምባሳደር ዲና ዛሬ ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በታንዛኒያ አቀባበል ሲደረግላቸው፡ ጥር 17/2013 ዓ.ም
ዛሬ ወደ ዲአር ኮንጎ ያቀኑት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ፣ በትላንትናው ዕለት ወደ ታንዛኒያ አቅንተው እስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እንዲለቀቁ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ከታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ማጉፉሊ ጋር
በተጨማሪም ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ስላካሄደዉ የሕግ ማስከበር ዘመቻ፣ አሁን እየተሰራ ስላለው የመልሶ ማቋቋምና የሰብዓዊ እርዳታ ተግባር ለፕሬዝዳንት ጆሴፍ ማጉፉሊ ገለጻ አድርገዋል፡፡