የአንካራው ስምምነት ለማደናቀፍ የሚሰሩ አካላትን በጋራ ለመከላከል ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ተስማሙ
በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት ከስምምነቱ ማግስት ግንኙነታቸውን ለማደስ በትብብር እንሰራለን ብለዋል
በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መክሯል
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የአንካራውን ስምምነት ተከትሎ ግንኙነታቸውን ለመሻሻል በጋራ አብረው ለመስራት ተስማሙ፡፡
በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ መሀመድ ኦማር የተመራ የፌደራል መንግስት ልዑክ በትላንትናው ዕለት አዲስአበባ ገብቷል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሶማሊያ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አብዱላሂ መሐመድ አሊ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ሁለቱ ሀገራት የአንካራውን ስምምነት ለማስፈጸም እና የስምምነት ሂደቱን ለማደናቅፍ የሚስሩ ያሏቸውን በስም ያልጠቀሷቸውን አካላት በጋራ ለመከላከል ቃል ገብተዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኤክስ (ትዊትር) ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ሁለቱ ሀገራ በጋራ ተግዳሮቶች፣ ዕድሎች እና ቀጣይ ትብብር ማዕቀፍ ዙርያ መሰናከሎችን እያለፍን መስራት እንደሚጠበቅብን ተስማምተናል ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ እና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ አሊ መሃመድ ኦማር በሁለቱ ሀገራት ቀጣይ ግንኙነት ዙርያ ውይይት ማደረጋቸው ተሰምቷል፡፡
በውይይቱ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባደሳደር ምስጋኑ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ህዝቦች የማይነጣጠል የጋራ ራዕይ ያላቸው መሆናቸውን በመግለጽ፤ ሀገራቱ ተባብሮ መስራት ፣ ችግሮች ሲጋጥሙም ተቀራርቦ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ አሊ መሃመድ ሶማሊያ የአንካራው ስምምነት በፍጥነት እንዲተገበር እንደምትፈልግ መግለጻቸውን አመላክተዋል፡፡
የአሁኑ የሶማሊያ መንግስት ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ መገኘትም ለስምምነቱ ተፈፃሚነት ሀገራቸው ያላትን ዝግጁነት እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ለሰላም መረጋገጥ እና ለጋራ እድገት የሶማሊያ መንግሰት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
ለአንድ አመት ያህል በዲፕሎማሲ ውዝግብ ውስጥ የከረሙት ሞቃዲሾ እና አዲስአበባ በቅርቡ በቱርክ አደራዳሪነት አንካራ በተደረገ ስምምነት ግንኙነታቸውን ለማደስ ቃል ገብተዋል፡፡