በአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛነት የተሾሙትን ሳተርፊልድን የሚተኩት አዲሱ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር አንካራ ገቡ
አፍሪካ ህብረትም በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ መሰየሙ ይታወሳል
ሳተርፊልድ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩ ሲሆን አሁን ጄፍሪ ፌልትማንን ተክተዋል
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን አዲስ ሹመት የተሰጣቸውን ዴቪድ ሳተርፊልድን የሚተኩት በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር አንካራ ገብተዋል፡፡
ሳተርፊልድ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩ ሲሆን አሁን ወደ አፍሪካ ቀንድ ኃላፊነት መምጣታቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ገልጸዋል፡፡ እርሳቸውን የሚተኩት ሴናተር ጄፍ ፍላክ ቱርክ መግባታቸውም ተሰምቷል፡፡
ዴቪድ ሳተርፊልድ ላለፉት ዘጠኝ ወራት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን ጄፍሪ ፌልትማንን በመተካት ነው የተሾሙት፡፡
ሳተርፊልድ ወደ አፍሪካ ቀንድ ኃላፊነት ሲመጡ በአንካራ የሚገኘው ኃላፊነታቸው ክፍት እንዳይሆን ደግሞ ሴናተር ጄፍ ፍላክ ተመድበዋል፡፡
በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደርነት የተሾሙት ጄፍ ፍላክ በአሪዞና የሪፐብሊካን ሴናተር ነበሩ፡፡ የጄፍ ፍላክ ሹመት ጥቅምት 16 በአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ጥቅምት 26 ደግሞ የሪፐብሊካን እና የዴሞክራት አባላት ባሉበት መጽደቁ ተገልጿል፡፡
አምባሳደር ጄፍ ፍላክ ከአንድ ወር በፊት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በተገኙበት ቃለ መሃላ መፈጸማቸውም ተገልጿል፡፡
ፍላክ የሪፐብሊካን ሴናተር ቢሆኑም የዴሞክራቱ ተወካይና የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደጋፊ እንደሆኑም ይነገራል፡፡
በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር በመሆን የተሾሙት ፍላክ ከአውሮፓውያኑ 2013 እስከ 2019 የአሪዞና ሴናተር በመሆን አገልግለዋል፡፡
አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ እንደ አዲስ ባዋቀረችው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኃላፊነት ለመጀመሪያ ጊዜ ፌልትማንን መሾሟ የሚታወስ ሲሆን እርሳቸውንም ከዘጠኝ ወራት የኃላፊነት ጊዜ በኋላ በዴቪድ ሳተርፊልድ ተክታቸዋለች፡፡
ከሰሞኑ በአስመራ እ በናይሮቢ ጉብኝት ያደረጉት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ቻይና ልክ አሜሪካ እንዳደረገችው ሁሉ በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እንደምትሰይም ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በአውሮፓውያኑ 2021 ከአሜሪካ በተጨማሪም የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በአህጉሩ ቀንድ አካባቢ ከፍተኛ ተወካይ የሚል አዲስ ኃላፊነት ያዋቀሩ ሲሆን የቀድሞውን የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆን መሾማቸው ይታወሳል፡፡