ግብጽና ሱዳን በዓመት 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ያገኛሉ- ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ
ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ ግድቡ በተለይም ሱዳንን ከጎርፍ አደጋ ይከላከላል ብለዋል
የግድቡ ሁለት የውሃ ማስተንፈሻዎች በሰከንድ 900 ሜትር ኪዩብ፤ በቀን 100 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ገደማ ውሃ ይለቃሉ
የአባይ ወንዝ የታችናው ተፋሰስ ሀገራት(ግብጽና ሱዳን) በህዳሴ ግድብ ሁለት የውሃ ማስተንፈሻዎች በዓመት 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚያገኙ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ተናገሩ።
ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ የግድቡን 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅን በማስመለክት ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው ይህንን የተናገሩት።
ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በዚሁ ወቅት በህዳሴ ግድብ ሁለት የውሃ ማስተንፈሻዎች በአማካኝ በአንድ ሰከንድ 900 ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚለቀቅ አስታውቀዋል።ይህም የግድቡ ሁለቱ የውሃ ማስተንፈሻዎች በቀን ውስጥ 100 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ገደማ የሚደርስ ውሃ እንደሚለቅ አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት የአባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በህዳሴ ግድብ የውሃ ማስተንፈሻዎች አማካኝነት በዓመት በአማኝ 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚለቀቅላቸውም ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ የኤልክትሪክ ለማመንጨት እና ለሌሎች ግልጋሎቶች ቢውልም፤ በተለይ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራ እንደ ውሃ ባንክ የሚያገለግል ነው መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህም የአባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በየዓመቱ የማይቆራረጥ እና የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸውም አረጋግጠዋል።
ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ አክለውም፤ የግድቡ የውሃ ሙሌት በክረምት ወቅት የሚከናወን እንደመሆኑ ሀገራቱን ከጎርፍ አደጋ እየተከላከለ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በዘንድሮው የውሃ ሙሌት ከፍተኛ የዝናብ መጠን በመኖሩ ግድቡ ቶሎ መሙላቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ይህም በተለይም ሱዳንን ከጎርፍ አደጋ ተከላክሏል ብለዋል።
አሁን ላይ ግን ግድቡ ሞልቶ በመፍሰሱ ሱዳናውያን የውሃ እጥረት ያጋጥመናል ከሚል አላስፈላጊ ስጋት ወጥተው ራሳቸውን ከጎርፍ አደጋ ሊጠብቁ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ውሃ ከመያዝ በዘለለ ለኢትዮጵያ ትልቁ ስኬት ሀይል ማመንጨት ነው ያሉት ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ፤ ለዚህም የሚሆን በቂ ውሃ ተይዟል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ለሀይል ማመንጨት ስራው የተርባይን ተከላዎች እየተጠናቀቀ ነው፤ ከትራንስፎርመር ጋር የማገናኘት ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ሀይል ማመንጨት ይጀምራል ሲሉመ ተናግረዋል።