“የህዳሴ ግድብ ሙሌት ተገባዶ ውሃው በግድቡ አናት ላይ ፈሶአል”- ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)
ይህን ለማሳካት የሚያስችል ውሃ መያዙንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት
የግድቡ ሁለት ተርባይኖች በቅርቡ ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ተብሏል
የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት ተገባዶ ውሃው በግድቡ አናት ላይ መፍሰሱን አስታወቁ፡፡
“ዛሬ ሀምሌ 12 ቀን 2013 ዓ/ም የሁለተኛውን አመት የህዳሴ ግድብ ሙሌት ተገባዶ ውሃው በግድቡ አናት ላይ ፈሶአል” ሲሉ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ያስታወቁት ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችም እንኩዋን ደስ አላችሁ” ሲሉ የደስታ መግለጫቸውን አጋርተዋል፡፡
“ይህ ውጤት ማለት 2 ተርባይኖችን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገውን የውሃ መጠንና ይዘናል ማለት ነው” ሲሉም ነው ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ያስቀመጡት፡፡
በዘንድሮው አመት እየዘነበ ያለው ውሃ መጠን እጅግ ከፍተኛ ነው ያሉም ሲሆን “ይህም ከፈጣሪ የተሰጠን ፀጋ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነና እንዴት እያገዘን እንደሆነ መረዳት እንችላለን:: ለዚሁም ምስጋና ይግባው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“እዚህ ደረጃ ለመድረስ በዘንድሮው አመት መጠነ ሰፊ ስራ ሰርተናል” ያሉት ኢ/ር ስለሺ “በቀጣይ ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ ብርቱ ስራዎች እየተሰሩ ነው፤ እናም ያንን በቅርብ ወራት በማጠናቀቅ ልፋታችንን ውጤት ላይ እናደርሳለን” ብለዋል፡፡
የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩን ኢ/ር ስለሺ በቀለን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ኢትዮጵያውያን በጉጉት የሚጠብቁትን ሙሌት ለማብሰር ጉባ ናቸው፡፡