ሱዳን የግድቡን የ2ኛ ዙር ሙሌት መጠናቀቅ አስመልክቶ ምላሽ ሰጠች
“ፖለቲካዊ ተነሳሽነቱ ካለ አሁንም ስምምነት ላይ ለመድረስ አልረፈደም”ም ነው ሚኒስትሩ ያለው
የመስኖ እና የውሃ ሀብት ሚኒስቴሯ ሱዳን አሁንም የኢትዮጵያን የተናጠል እርምጃ እንደማትቀበል አስታውቋል
ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት አጠናቃ መሙላቷን ተከትሎ ሱዳን ምላሽ ሰጠች፡፡
የሃገሪቱ የመስኖ እና የውሃ ሀብት ሚኒስቴር ሱዳን አሁንም የኢትዮጵያን የተናጠል እርምጃ እንደማትቀበል አስታውቋል፡፡
የወንዙን ሃገራት ፍላጎትና ስጋት ከግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ ጉዳዩን ያለቀለት አድርጎ በማሰብ ኢትዮጵያ በተናጠል ወስዳዋለች ያለውን እርምጃ እንደማይቀበልም ነው የገለጸው፡፡
የሁለቱን ወዳጅ ሃገራት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ይጎዳል ካለው ከዚህ አካሄድ ውጪ በእምነት መደራደር፣ የሁሉንም አካላት ፍላጎት በዋናነትም የሮዜሪዬስን ግድብ ጉዳይ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ከአስገዳጅ ስምምነት መድረስ የተሻለው አማራጭ እንደሆነም አስቀምጧል፡፡
“ፖለቲካዊ ተነሳሽነቱ ካለ አሁንም ስምምነት ላይ ለመድረስ አልረፈደም”ም ነው ሚኒስትሩ ያለው፡፡
በግድቡ የሁለተኛ ዙር ሙሌት ሊደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል ስራ ለወራት በሚመለከታቸው አካላት ሲሰራ እንደነበር ሱዳናውያን ይወቁልኝም ብሏል፡፡
በሮዜሪዬስ እና በጀበል አወሊያ ግድቦች አስፈላጊው ቴክኒካዊ የጥንቃቄ እርምጃ ባይወሰድ ኖሮ በመጠጥ ውሃ እና በኤሌክትሪክ አቅርቦት ላይ የከፋ ጉዳት ይደርስ እንደነበርም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
ልክ እንደ ግብጽ ሁሉ በግድቡ የድርድር ሂደት አስገዳጅ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ፍላጎት ያላት ሱዳን በድርድሩ የሌሎች አካላት ተሳትፎ እንዲኖር ደጋግማ መጠየቋ የሚታወስ ነው፡፡