መንግስት “በሰብአዊ እርዳት ላይ ታጥረው” የማይሰሩ የተመድ ድርጅቶችን ከሀገር ሊያስወጣ እንደሚችል ገለጸ
የፌደራል መንግስት ከ8 ወራት በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ትግራይን ለቆ መውጣቱ ይታወሳል
በመንግስትና በህወሃት ኃይሎች መካከል ያለው ግጭት አሁን ላይ በአማራና ትግራይ ክልል ድንበር ላይ ሆኗል
የኢትዮጵያ መንግስት እንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች በተለይም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የኢትዮጵያ መንግስትን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ የማንኳሰስና የማጠልሸት ፕሮፓጋንዳ እየሰሩ መሆናቸውን ገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሚኒስትር ዲኤታ ሬድዋን ሁሴን ባስተላለፉት መልእክት ከእርዳታ ይልቅ ፕሮፓጋንዳ በመስራት የኢትዮጵያን መንግስት የማዋከብና የማጠልሸት ዘመቻ በሰፊው እየሰሩ ነው፤መንግስት ይህ እንዲቆም ማስጠንቀቁንም ገልጸዋል፡፡
መንግስት ድርጅቶቹ የኢትዮጵያን መንግስት በማዋከብ የሚቀጥሉ ከሆነ መንግስት “ከአንዳንዶቹ ጋር አብሮ የመስራቱን ጉዳይ እንደሚያጤነው” የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው “እንዳንዶቹንም ከሀገር ለማስወጣት የሚችልበት ምቹ ሁኔታ” ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
አቶ ሬድዋን ተመድና ሌሎች ኢትዮጵያን እረዳለሁ የሚል በእርዳታ ላይ ውይም በሰብአዊ እርዳታ ላይ ታጥሮ መንቀሳቀስ ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት አንዳንድ የሰብአዊ መብት አስተባባሪዎች ለሌላኛው ወገን ድጋፍ በማድረግ ቀውሱ እንዳይቆም የሚያደርጉበት መንገድ ይኖራል፤ በኢትዮጵያ ባለፉት 8 ወራት ይህ ተስተውሏል ብለዋል፡ መንግስት ይህ ተግባር እንዲቆም ሲያሳስብ ቆይቷል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው፡፡
አቶ ሬድዋን አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት፣ግለሰብ ባለስልጣናት የመንግስትን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ማበረታት ሲኖርባቸው መንግስት ትግራይ ክልል እያለ ሲያሰሙት የነበረውን ተመሳሳይ ወቀሳ እያሰሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ተኩስ አቆም እያለ የህወሃ ት ኃይሎች አሁንም በአማራ ክልል አካባቢ ተኩስ ከፍተዋል፤መንግስት ተኩስ አቁም ያወጀው ለህዝቡ ሰላም የመስጠት ሲል እንጅ የግጭት ቦታ ለመቀየር አልነበረም በማለት ምእራባውያን በህወሃት ላይ ያላቸውን አቋም ተችተዋል፡፡
የፌደራል መንግስት ጥቅምት 24፣2014 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ካሳወቁ በኋላ በትግራይ ክልል “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በመጀመሩ ግጭቱ መከሰቱ ይታወቃል፡፡
ለ8 ወራት የቆየው ግጭት በፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈታ በሚል የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ መንግስት መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወቃል፡፡ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው በትግራይ ሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል ለሚሉ አካላት ለማሳየትና ተጨማሪ ኪሳራ ሳይደርስ የትግራይ ቀውስ በውይይት እንዲፈታ በማቀዱ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የመንግስት ጦር መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌንና ሌሎች ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ሮይርስ ዘግቦ ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ የህወሓት ኃይሎች ለወራት በአማራ ክልል ስር የነበሩት ኮረምና አላማጣን መቆጣጠራቸውም ተዘግቦ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስት በትናንትናው እለት በሰጠው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች “ በራያ አካባቢ አላማጣ፣ ኮረም እና ባላ፤ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፃግብጅ፣ዛታ እና አበርገሌ እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ እና ማይጠብሪ ዳግም ወረራ ከፍቶብናል” ስለሆነም ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግረናል ሲል አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ቃል አቀባይ ግዛቸው ሙሉነህ የኦሮሚያ ክልል መንግስትን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች ተደቅኖብናል ያሉትን የህልውና አደጋ ለመከላከል ጥሪውን መቀበላቸውን አስታውቋል፡፡
የኦሮሚያ ክልልና የሲዳማ ክልል የጸጥታ ሃይሎች መከላከያ ሰራዊቱን ለማገዝ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ መንቀሳቀሳቸውን የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡