በትግራይ ውጤታማ የተኩስ አቁም እንደሚተገበር እምነት አለኝ- አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ ተወያይተዋል
በክልሉ ላለው ችግር የፖለቲካ መፍትሄ እንዲገኝም ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጥሪ አቅርበዋል
በትግራይ ክልል ውጤታማ የተኩስ አቁም እንደሚተገበር እምነት እንዳላቸው የተባሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።
ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ መነጋረቸውን በትዊተር ገጻቸው ባወጡት መረጃ አስታውቀዋል።
“በትግራይ ክልል ውስጥ ውጤታማ የሆነ የተክሱ ማቆም ይጀመራል የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል ጉቴሬዝ በመልእክታቸው ፡፡
ሲቪሎች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያታወቁት ዋና ጸሃፊው፤ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች በአፋጣኝ ሊደርስ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
በክልሉ ላለው ችግርም ከወታደራዊ ይልቅ የፖለቲካ መፍትሄ እንዲገኝም ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጥሪ አቅርበዋል።
የፌዴራሉ መንግስት ወቅቱን የሚመጥን ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል በሚል በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥያቄ በአዎንታ መቀበሉን በዛሬው እለት አስታውቋል።
በዚህም መሰረት አሁን የተጀመረው የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ያለቅድመ ሁኔታ በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ከዛሬ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ጀምሮ ማወጁንም ነው ይፋ ያደረገው።