ሱዳን በግድቡ ጉዳይ 4 አለምአቀፍ አደራዳሪዎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበች
ሳኡዲ አረቢያ በግድቡ ጉዳይ ሶስቱ ሀገራት ሰላማዊ መፍትሄ ላይ እንዲደርሱ ጥረት አደርጋለሁ ብላለች
ሱዳን በአደራዳሪነት ይግቡ ያለቻቸው አካላት አሜሪካ፣ተመድ፣ የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት ናቸው
ሱዳን በኢትዮጵያ ግድብ ድርድር ጉዳይ አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ)፣ የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርባለች፡፡
ሱዳን እያንጸባረቀችው ያለው አቋም ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ቀደም ሲል በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት፤ በአሜሪካና በአውሮፓ ህብረት ታዛቢት ድርድሩ እንዲካሄድ የደረሱትን ስምምነት የሚቃረን ነው፡፡ ሱዳን ይህን ጥሪ ያቀረበችው የሱዳን የግድቡ ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚቴ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር ከተወያየ በኋላ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
በስብሰባው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የመስኖና የውሃ ሃብት ሚኒስትር፣ የደህንነት ሰዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር መገኘታቸው ተገልጿል፡፡ ተሰብሳቢዎቹ በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ ያለውን ችግርና የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነት ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኮንጎ መቀየሩን ተወያይተውበታል፡፡
ስብሰባውን ተከትሎ በወጣው መግለጫ አራቱ አካላት ማለትም አሜሪካ ፣ የተባበሩት መንግስታት ፣ የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት ከታዛቢነት ይልቅ የአደራዳሪነት ሚና እንዲኖራቸው ሱዳን ጠይቃለች፡፡
በስብስባው ላይ የሚመለከታቸው ኤጀንሲዎች የህዳሴው ግድብ ሙሌት በኤሌክትሪክ አገልግሎትና በመስኖ ልማት ላይ ሊያደርስ የሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም መክረዋል ተብሏል፡፡
በስብሰባው ላይ ለአራቱ አለምአቀፍ አካላት አደራዳሪ ሁኑ የሚለውን ሃሳብ ለማሳወቅ ተስማምተዋል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ በህዳሴው ግድብ ጉዳይ
በትናንትናው እለት የሳዑዲ አረቢያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አህመድ ቢን አብዱል አዚዝ ካታን ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ በሰጡት መግለጫ ሳዑዲ ሶስቱን ሀገራት ሊያስማማ የሚችል መፍትሄ እንዲገኝ ጥረት እንደምታደርግ አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው የሳዑዲው ንጉስ ሳልማን በግድቡ ጉዳይ መፍትሄ ለማምጣት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ የሳዑዲ ባለስልጣናት ከዚህ በፊት ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲና ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በግድቡ ጉዳይ ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል፡፡