በግድቡ ዙሪያ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቷ ተገለጸ
ከሰሞኑ በካይሮ ፣ አስመራ እና ካርቱም ጉብኝት ያደረጉት አምባሳደር ፌልትማን በኢትዮጵያም የሥራ ጉብኝት ላይ ናቸው
በአፍሪካ ቀንድ ለአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ስለ ግድቡ ማብራራታቸውን ዶ/ር ስለሺ በቀለ ገልጸዋል
በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት እና በአፍሪካ ሕብረት መራሹ የሦስትዮሽ ድርድር ዙሪያ ከአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን እና ከልዑካቸው ጋር ግልፅ የሁለትዮሽ ውይይት ማካሔዳቸውን የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ ፣ ዓባይን መጠቀም ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ እና ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚከናወኑ ተግባራትን ለመልዕክተኛው ማስረዳታቸውንም ነው የገለጹት፡፡
አምባሳደር ፌልትማን ሦስቱ ሀገሮች በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ላይ እንዲደርሱ ለመርዳት የሀገራቸውን ቅን እና ገለልተኛ ድጋፍ እንዲሁም ጠንካራ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል ሲሉም በትዊተር ገጻቸው አብራርተዋል፡፡
ከሰሞኑ በካይሮ ፣ አስመራ እና ካርቱም ጉብኝት ላይ የነበሩት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ዛሬ ከውሃ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ጀምረዋል፡፡
ዲፕሎማቱ ከሰሞኑ ከግብፅ ፣ ከኤርትራ እና ከሱዳን መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎችም ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
በጆ ባይደን አስተዳደር በቅርቡ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሸሙት አምባሳደር ፌልትማን በቀጣናው ያሉ አለመግባባቶች ፣ በተለይም የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ እና የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ውዝግብ ፣ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ለማድረግ በሀገራቸው ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡
አምባሳደሩ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ሦስቱም ተደራዳሪ ሀገራት ካልፈቀዱ በስተቀር አሜሪካ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላትም ነው የገለጹት፡፡