መንግስት ከሚያቀርባቸው 362 መሰረታዊ መድሃኒቶች ውስጥ በሀገር ውስጥ የሚመረቱት 97 መሆናቸውን አገልግሎቱ ገለጸ
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢያ አገልግሎት በመጪዎቹ 3 አመታት የሀገር ውስጥ የመድሀኒት ምርት አቅርቦትን ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብሏል
የኢትዮጵያ የመድሀኒት እና የህክምና መገልገያ አምራቾች ማህበር የውጭ ምንዛሬ እና የግብአት እጥረት የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርት የሚፈለገውን ያህል እንዳያድግ ማድረጉን ገልጿል
ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ ከምታስገባቸው ምርቶች ነዳጅ ፣ ማዳበርያ እና ሌሎችም ወሳኝ ምርቶች መካከል መድኃኒት አንዱ ነው፡፡
ምርቱን በዋናነት ከህንድ ቻይና ሌሎችም ሀገራት ተገዝቶ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ከፍተኛ ምንዛሪን የሚጠይቅ ነው፡፡
በ2014 ዓም በሀገር ውስጥ በሚመረቱ መድሀኒቶች እና የህክምና ግብአቶች ከአጠቃላይ ፍላጎቱ አንጻር የነበራቸው ሽፋን 8 በመቶ ብቻ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና የጤና ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የመድኃኒት እና የህክምና ግብአት አምራቾች የሚፈጸም ግዥን በሚቀጥሉት 3-5 አመታት እስከ 70 በመቶ ለማድረስ ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ዘርፉ አሁንም የውጭ ምንዛሪ፣ የማስኬጃ በጀት እንዲሁም የግብአት እጥረት እንዳለበት ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በ2016 በጀት አመት በመድኃኒት ፣ የህክምና መሳሪያዎች እና መገልገያዎችን፣የላቦራቶሪ ኬሚካሎችን ጨምሮ በጥቅሉ ከ29 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የህክምና ግብአቶችን ገዝቼ አከፋፍያለሁ ብሏል፡፡
በአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወል ሀሰን ባለፈው አመት 5 ሺህ ለሚጠጉ የመንግስት ጤና ተቋማት 29 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው መድኃኒቶችን እና የህክምና ግብአቶችን ማዳረስ እንደተቻለ ለአል ዐአይን አማረኛ ተናግረዋል፡፡
በዚህም አጠቃላይ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት 36 በመቶ መሸፈን መቻሉን የሚያነሱት ዳይሬክተሩ በሀገር ውስጥ የሚሸፈኑ የመድኃኒት አይነቶች ከፍላጎቱ አንጻር አሁንም በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወል እንደሚሉት “እስካሁን ባለው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ከሚፈልጉት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲሁም ሀገር ውስጥ እስከሚደርሱ ከሚወስዱት ጊዜ አንጻር ባለፉት አመታት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን እንገኛለን፡፡
ለዚህም ገብአቶችን ለማሟላት ከሚያስፈልጋቸው የውጭ ምንዛሪ 55 በመቶውን ለመሸፈን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋጋር ወደ ተግባር ተገብቷል፤ ይህም የምርት አቅማቸው እንዲያድግ አድርጓል፡፡”
ከዚህ ቀደም በጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር የሀገር ውስጥ አምራቾች ከአቅማቸው 25 በመቶ ያህሉን ብቻ ሲጠቀሙ መቆየታቸው ይነገራል፡፡
በአሁኑ ወቅት 97 የሚጠጉ የመድሀኒት አይነቶች በሀገር ውስጥ አምራቾች የሚቀርቡ ሲሆን አጠቃላይ ዋጋቸውም 5 ቢሊየን ብር ድረስ የሚያወጡ ናቸው፡፡
የህክምና ቁሳቁሶችን ሳይጨምር መሰረታዊ የሚባሉ 362 በላይ መድሀኒቶች በመንግስት እየቀረበ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ አወል፤ በሀገር ውስጥ አቅርቦት በአይነት እና በመጠን ባለፉት ቅርብ አመታት በርካታ መሻሻሎች ቢታይበትም ከገበያው ፍላጎት አንጻር አሁንም ብዙ እንደሚጠበቅበት ይናገራሉ፡፡
“አገልግሎቱ በአጠቃላይ 1020 መድኃኒቶች እና የህክምና ግብአቶች ለሀገር ውስጥ መሰረታዊ እንደሆኑ በዝርዝር ውስጥ ያካተታቸው ናቸው፤ ከዚህ ውስጥ ከ200 በላይ የሚሆኑት ምንም አቅራቢ የሌላቸው ናቸው። የዓለም አቀፍ መድኃኒት አቅራቢዎች ብዛት 185 ቢሆንም አሁንም በሀገሪቱ ያለውን የመድኃኒት አቅርቦትና ፍላጎት ማጣጣም አልተቻለም” ብለዋል፡፡
ዶክተር ዳንኤል ዎክቶሌ የኢትዮጵያ የመድሀኒት እና የህክምና መገልገያ አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉ ከባንክ አሰራር እና ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ዘርፉ የሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች በበቂ ሁኔታ መፈታት ከተቻለ የሀገር ውስጥ አምራቾች የህክምና ግብአቶችንም ሆነ መድኃኒቶችን ለማምረት ጥሩ አቅም ገንብተዋል፡፡
“የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት 55 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ከመንግስት እንድናገኝ አድርጓል፤ ነገር ግን የቀረውን ገንዘብ ከባንኮች ለማግኝት በምናደርገው ጥረት አንዳንድ ጊዜ በቂ ምንዛሪ አናገኝም፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ምንዛሪውን ለማግኝት ገቢ እንዳናደርግ የምንጠየቀው ገንዘብ እጥረትም በተፈለገው ልክ እንዳንቀሳቀስ አድርጎናል፡፡”
ክትባቶችን ጨምሮ የቲቢ እና የኤችአይቪ መድሀኒቶች በዋናነት ከውጭ በድጋፍ እና በግዥ የሚቀርቡ ናቸው፤ ከዚህ ውጪ ያሉ መሰረታዊ የሚባሉ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸውን መድኃኒቶችን እና የህክምና ግብአቶችን የሚያመርቱ በኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የህክምና መገልገያ አምራቾች ማህበር ውስጥ የታቀፉ 24 አምራቾች ይገኛሉ፡፡
ከነዚህ መካከል 12ቱ መድሀኒቶችን ብቻ የሚያመርቱ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ግብአቶችን እና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን የሚያመርቱ መሆናቸውን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ገልጸዋል፡፡
የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገሩት ፕሬዝዳንቱ “አሁን ላይ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው መገልገያ የሚገባው ከውጭ ሀገር ነው፤ ይህንን ለመቅረፍ የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ነድፈናል፤ ይህ እቅድ በመሳርያዎች ላይ ያለውን እጥረት ለመፍታት ፣ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ ፣ ሀገር ውስጥ ተሰርተው ለአገልግሎት ብቁ ሊሆኑ የሚችሉ እና ከውጩ የሚገቡትን ማሰቀረት ላይ አላማ ያደረገ እቅድ ነው” ብለዋል፡፡
ሌላው ማህበሩ እየሰራሁበት ነው ያለው ሀገር በቀል የባህል ህክምና እና መድኃኒቶችን ወደ ዘመናዊ ሂደት ማስገባትን ይመለከታል፡፡
በዚህ ረገድ ከጤና ሚኒስቴር እና ከባህል ህክምና ማህበራት ጋር በተደረሰ መግባባት ባህላዊ መድሀኒቶችን ወደ ምርት ለማስገባት የመገባብያ ስምምነት ተፈጽሟል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የደረሱ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን መስተጓጎል ለማስተካከል ከአለም አቀፍ እና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ከሚያደርገው ትብብር በተጨማሪ የአየር ትራንስፖርቶችን በመጠቀም በዋናነት የሰላም መደፍረስ ባጋጠመባቸው በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የአቅርቦት ስርጭችቱን እያከናወንኩ ነው ብሏል፡፡