የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሸ ድርድርን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስጀመር እንደሚቻል ዲ.አር ኮንጎ ገለፀች
በኢትዮጵያ በማንኛውም ጊዜ በድርድሩ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች
ም/ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ዲ.አር ኮንጎ አቻቸው ክርስቶፌ ሉቱንዱላ ጋር ተወያይተዋል
የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሸ ድርድርን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስጀመር እንደሚቻል ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ገልጻለች።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻቸው ክቡር ክርስቶፌ ሉቱንዱላ ጋር ውይይት አድርገዋል።
- የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ቱኒዚያ ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች
- በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች በውይይት መፈታት አለባቸው- የተመድ የጸጥታው ም/ቤት
ውይይታቸው በአፍሪካ ህብረት አስተባበሪነት የሚካሄደውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ እንደነበረ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
በውይይቱም አቶ ደመቀ፤ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ሂደት ላይ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት ለተጫወተችው አዎንታዊ የመሪነት ሚና አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በመቀጠልም የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝት ገልጸው፣ ይህም በሁሉም አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ላይ መድረስ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
አያይዘውም ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲሰፍን በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ጽኑ ፍላጎት ገልጸው፣ ናይል የተፋሰሱ አገራት የትብብር እንጂ የግጭት መንስዔ መሆን እንደማይገባውም አንስተዋል።
አቶ ደመቀ አክለውም፤ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ሂደት እስካሁንም ድረስ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ላይ በመድረስ ተጨባጭ ውጤት ያስመዘገበ መሆኑን አውስተው፤ በቀጣይም ሂደቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስቀጠል የሁሉንም ወገኖች ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ መፍትሔ ላይ መድረስ አንደሚቻል ኢትዮጵያ በፅኑዕ ታምናለች ብለዋል።
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፌ ሉቱንዱላ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተሳካ አገራዊ ምርጫ በማካሄዷ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ቀጥለውም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ላሳየችው ቁርጠኝት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህን አጥብቃ የምታምን መሆኑና ጠቅሰው፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድርም በዚሁ መርህ መመራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የሶስትዮሸ ድርድሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስጀመር የሚቻል ስለመሆኑም አንስተዋል ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት።