የግድቡ ውሃ የመያዝና ኃይል የማመንጨት ስራ በተቀመጠለት ጊዜ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ገለጹ
የግድቡ ውሃ የመያዝና ኃይል የማመንጨት ስራ በተቀመጠለት ጊዜ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ገለጹ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ መሰረት ሳይስተጓጎል እየተከናወነ መሆኑን የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ሰብሳቢ እና የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሀም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ሚኒስትሩ የግድቡን ግንባታ ፕሮጄክት ጎበኝተዋል፡፡ ግንባታው በተያዘለት እቅድ መሰረት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም ሳይስተጓጎል እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሩ “በራሳችን ስንፍና የፈጠርናቸውን ችግሮች ከለውጡ በኋላ በፍጥነት በማረም ወደ መስመር አስገብተን መስራት ቀጥለናል” ብለዋል፡፡
“ችግሮችን አስተካክለን መስራት በጀመርንበት ወቅት ከግብፅ ጋር ስናደርገው የነበረው ድርድር መልኩን ቀይሮ ሂደቱን የማደናቀፍ ጥረትና ሙከራ ቢያጋጥምም፣ በሉዓላዊነቱ እና በሃብቱ የማይደራደር ህዝብና መንግስት ስላለን የግንባታ ሂደቱ ለአፍታም ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ተደርጓል” ሲሉ ገልጸዋል።
አብርሀም በላይ (ዶ/ር) በግድቡ ጉብኝት ላይ
“ዓለም አቀፉን የኮረና ወረርሽኝ በሚገባ እየተከላከልን ግንባታውን ለህዝባችን በገባነው ቃል መሰረት ለማጠናቀቅ በግንባር ከተሰለፉ ዜጎቻችን እና የውጭ የስራ ተቋራጮች ጋር በመሆን ሃያ አራት ሰዓት ያለ እረፍት እየሰራን እንገኛለንም” ብለዋል።
“የገጠሙንን እና የሚገጥሙንን ፈተናዎች በመወጣት ውሃ የመያዝ ስራን፣ የቅድመ ማመንጫ እና የፕሮጀክቱ ማጠቃለያ ስራ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እናከናውናለን” ማለታቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በግድቡ ግንባታ ላይ መፍጠን ያለባቸውን አስፈላጊ ስራዎችን በመገምገም የማሻሻያ ውሳኔዎችን መደረጋቸውን ደግሞ የውኃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ኢ/ር) ገልጸዋል፡፡ በህዳሴ ግድብ የግንባታ ቦታ ጉባና ሰዳል ከሚመለከታቸው የመንግስት፣ የተቋራጮችና አማካሪዎች የስራ ሀላፊዎች ጋር የስራ ግምገማና ጉብኝት ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ኢ/ር) ግድቡን ጎብኝተዋል
ሚኒስትሩ ስራው እየተፋጠነ እንደሚገኝ ገልጸው በመጪው ክረምት የመጀመሪያ አመት ውሃ ለመያዝ የሚያስችለው ዝቅተኛው ብሎክ ከ525ሜ ከፍታ ወደ 534ሜ ያደገ ሲሆን እሰከ ሰኔ መጨረሻ ሳምንት 572ሜ እንዲደርስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ላለፉት 5 ዓመታት 525ሜ ላይ ከነበረበት ወደሚፈለገው ደረጃ የማሳደጉ ስራ ግድቡ በቅርቡ ውሃ መያዝ ስለመቻሉ ብርቱ ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ውጤት ለመድረስ ወደ ኋላ የሚመልስ ነገር እንደሌለ ነው በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት፡፡ ሌሎች ተግባራት ማለትም የብረት ስራዎች፣ የትላልቅ ውሃ ማስተላለፊያ በሮች ተከላ፣ የተርባይንና ጀነሬተሮች ተከላ ወዘተ በእቅድ እተሰራ ነውም ብለዋል ዶ/ር ስለሺ፡፡ በግድቡ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ ላሉ ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡