የህግ ምሁራን ምርጫ ማካሔድ ባለመቻሉ ስለቀረቡት አማራጮች ምን ይላሉ?
የህግ ምሁራን ምርጫ ማካሔድ ባለመቻሉ ስለቀረቡት አማራጮች ምን ይላሉ?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ምርጫ ይደረጋል ብሎ የጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡ ይህ ደግሞ የምርጫው ሂደት ከሕገ መንግስቱ ጋር እንዳይጣረስና አሁን ያለው ምክር ቤት የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት ለማድረግ የሚያስችል ቀነ ገደብ ነበር፡፡ ይሁንና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ቦርዱ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል አስታውቋል፡፡ይህንን ተከትሎም በኢትዮጵያ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ይደረጋል ከሚለው የሕገ መንግስት ድንጋጌ ጋር የሚጣረሱ ሁናቴዎች እዳይፈጠሩ ያሰጋል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት የፊታችን መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም የሥልጣን ጊዜው የሚያበቃ በመሆኑ ቀጣይ ምርጫ ተደርጎ መንግስት መመስረት የሚቻለው እንዴት ነው የሚለው ጉዳይ የሃገሪቱን ፓርቲዎችና ምሁራንን እያነጋገረ ይገኛል፡፡
ይህንኑ ጉዳይ የሚመለከት ውይይት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ተካሂዷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ኮቪድ-19፣ ምርጫን ማራዘም እና የህግ አማራጮች” በሚል ርዕስ በተደረገው ውይይይት ላይ ቀጣይ እንደ ሀገር እና እንደ መንግስት በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ውይይቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአማራጮቹ ዙሪያ ሲያወያዩ
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምክትል አቃቤ ህግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫውን በሚቀጥለው ነሃሴ 2012 ዓ.ም ለማድረግ ወስና ዝግጅት የጀመረች ቢሆንም በኮሮና ቨይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫውን በታቀደው መርሃ ግብር መሰረት ለማድረግ እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡
ይህንንም ችግር ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ጠብቆ ለመፍታት በሦስት ቡድኖች የተደራጀው የህግ ባለሙዎች ቡድን አራት አማራጭ መንገዶችን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቧል ብለዋል፡፡
የቀረቡት አማራጭ መንገዶች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ሕገ መንግስት ማሻሻል እና የሕገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉ ናቸው፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
ከአራቱ የቱ ያዋጣል?
የህግ አማካሪና ጠበቃ ሞላልኝ መለሰ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን የሚለውን አማራጭ ለማድረግ “ምክር ቤቱ ሥራውን በአግባቡ ማከናወን ካልቻለና አስቸጋሪ ሁኔታ ከተፈጠረ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤቱን አስፈቅደው ሊበትኑት ይችላሉ፤ ይህ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመው ታዲያ ምክር ቤቱ ውስጥ ስራን ማከናወን የሚያስችል ሁኔታ ሲጠፋ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ግን አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ነው ያነሱት፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና ፌዴራሊዝም መምህርና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁናቴ ላይ አስተያት በመስጠት የሚታወቁት ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር) ከቀረቡት አማራጮች መካከል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅና ምክር ቤቱን (የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን) መበተን አዋጭ እንዳልሆኑ ይገልጻሉ፡፡
የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 60 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሔድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል›› ይላል። ታዲያ አሁን የቀረበው አማራጭ ምርጫውን ለማካሄድ ሳይሆን ጭራሽ ለማራዘም በመሆኑ የሚያስኬድ አይደለም ይላሉ፡፡ ሌላው ምክንያታቸው ደግሞ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 60 ንዑስ አንቀጽ 5 ነው፡፡ ንዑስ አንቀፁ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተበተነ በኋላ ሀገሪቱን የሚመራው ሥልጣን ይዞ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራ የዕለት ተዕለት የመንግሥት ሥራ ከማከናወንና ምርጫ ከማካሔድ በስተቀር አዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችንና ድንጋጌዎችን ማውጣት ወይም ነባር ሕጐችን መሻርና ማሻሻል አይችልም›› ይላል፡፡
ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)
ዶ/ር ሲሳይ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማውን ከበተኑ የሚኖረው መንግስት ደካማ ነው የሚሆነው፤ መወሰን፣ህጎችን ማውጣትና ማሻሻል፣ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ማድረግ አለመቻሉ በጣም ደካማና ልፍስፍስ መንግስት ያደርገዋል፤ በመሆኑም የዕለት ከዕለት ስራዎችን ብቻ የሚሰራ መንግስት ብቻ ነው የሚሆነው ይላሉ፡፡ በመሆኑም አዋጭ አይደለም፡፡
አቶ ሞላልኝም ከላይ ዶ/ር ሲሳይ ያነሱትን ሃሳብ ይደግፋሉ፡፡ ባለሙያው ‹‹በሕገመንግስቱ አንቀጽ 60 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን አድርገው በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ አዲስ ምርጫ እንዲከናወን ማድረግ ነው ቢልም ምክር ቤቱን ለመበተን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክንያት ምን መሆን አለበት የሚለው ግን ትልቅ ጥያቄ ነው›› ይላሉ፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ያለውን የዲሞክራሲ ልምምድ እያሰፋን እና እያሳደግን ብሎም እያዳበርን መሄድ ካለብን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ምክር ቤቱ በራሳቸው ፍላጎት ይህን አይነት ውሳኔ ለመስጠት ስልጣን ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ማከናወን አልተቻለም ብለው የስልጣን ዘመኑ ያለቀውን ምክር ቤት በትኖ ለስድስት ወር ለገዢው ፓርቲ ስልጣን እንዲሰጥ እንዲጠይቁ ማድረግ እና ምክር ቤቱም የሌለውን የስልጣን ዘመን ለገዢው ፓርቲ እንዲሰጥ ማድረግ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ በመሆኑም ከላይ ከላይ ሲታይ ይህኛው አማራጭ ቀላል ምርጫ ቢመስልም የሚያስከትለው ፖለቲካዊ ቀውስ ከባድ ሊሆን ስለሚችል የተሻለ አማራጭ አይደለም›› በማለት ይገልጻሉ፡፡
አቶ ሞላልኝ መለሰ
በምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የቀረበው ሌላኛው አማራጭ ሕገመንግስቱን ማሻሻል ሲሆን የህግ ባለሙያዎች በዚህም ዙሪያ ምሁራዊ ዕይታዎችን አስቀምጠዋል፡፡
አቶ ሞላልኝ የተፈጠረውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ችግር ለአንድ ጊዜ ብቻ ለመፍታት በሚያስችል ሁኔታ በሕመንግስቱ አንቀጽ 105 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ሕገመንግስቱን ማሻሻል የተሻለ ሕገ መንግስታዊ መሰረት እንዲኖረው ስለሚያደርግ የተሻለው ሰላማዊ አማራጭ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ዶ/ር ሲሳይ በበኩላቸው ሕመንግስቱን ማሻሻል በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ፣ ሁሉም በሚሳተፍበት ሂደት እንዲሁም ምርጫ ከመቃረቡ በፊት ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ከሆነ ቀደም ማለት እንዳለበት ያነሱት ባለሙያው አሁን ላይ ግን ግዴታ ውስጥ ተገብቶም ቢሆን ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
ሕገመንግስቱን ለማሻሻል የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ የማሻሻያ ሀሳቡን በ2/3ኛ ድምጽ ማፅደቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ አባላት ክልሎች መካከል 2/3ኛ የሚሆኑት ክልሎች ምክር ቤቶች ሀሳቡን በድምጽ ብልጫ ሊያፀድቁት ይገባል፡፡ ይህን የማሻሻያ ሀሳብ ወደ ውይይት ለማቅረብ ሀሳቡ ከሕዘብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት በ2/3ኛ ድምጽ ወይም ከፌዴሬሽኑ አባላት ክልላዊ መንግስታት ምክር ቤቶች በ1/3ኛው አባላት በድምጽ ብልጫ ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ አዋጁ ከታወጀ በኋላ ምርጫ ማድረግም የሥነ ልቦና ጫና እንዳለው ዶ/ር ሲሳይ ሲገልጹ አቶ ሞላልኝ ደግሞ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ሌላው አማራጭ ነው ይላሉ፡፡ ይሁንና የሽግግር መንግስት ማቋቋም በኢትዮጵያ ካሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት እና የብስለት ደረጃ እንዲሁም ሀገራዊ ኃላፊነትን ለመሸከም ካላቸው የአቅም ውስንነት እና ከሁሉም በላይ ፅንፍ የያዘ አቋምን በማራመድ ካላቸው ልምድ አንጻር ሃገሪቱን ወደ ተወሳሰበ ችግር ከማስገባት ያለፈ ውጤት እንደማይኖረው ያነሳሉ፡፡
የህግ ባለሙያዎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማወጅ እና ፓርላማን መበተን የሚሉት አማራጮች ከአወንታዊ ይልቅ አሉታዊ ጎናቸው እንደሚያመዝን አንስተዋል፡፡
ዶር ሲሳይ አሁን ላይ የሕገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ የሚለው የተሻለ ነው ሲሉ አቶ ሞላልኝ ደግሞ ሕገመንግስቱን ማሻሻል የተሻለ ሕገ መንግስታዊ መሰረት እንዲኖረው ስለሚያደርግ የተሻለው ሰላማዊ አማራጭ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዛሬ በቀረቡት አማራጮች ዙሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን አስተያየቶችን መስጠታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ለአብነትም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግን የተሻለ አማራጭ አድርጎ መርጧል፡፡ ሁሉንም አማራጮች ያልተቀበለው አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) ደግሞ እንዲህ ዓይነት ሕገ-መንግስታዊ ቀውስ ሲፈጠር ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት በተለየ ሁኔታ በህግ መብት የተሰጠው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም መንግስታዊ ተቋም ስለሌለ የተፈጠረውን ሕገ-መንግስታዊ ቀውስ እንዴት እንፍታው? በሚለው ጥያቄ ተነጋግሮ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክከር ሂደት (National Dialogue) መጥራት ያስፈልጋል ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባል አቶ ጃዋር መሀመድም እንዲሁ ሁሉም አማራጮች ተቀባይነት እንደሌላቸው በፌስቡክ ገጹ አብራርቶ ለሕገ መንግስታዊ ቀውሱ ፖሊቲካዊ እንጂ ህጋዊ መፍትሄ ሊኖር እንደማይችል ገልጿል፡፡
በቀጣይም በጉዳዩ ላይ ውይይቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡