“ብልጽግና ምርጫውን ብቻውን ልምራው ካለ ውጤቱ ወደ ከፋ ችግር ይከተናል”-ህወሓት
“ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አራት ዋና ዋና ፈተናዎች ተጋርጠውባታል” ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተጋረጡባትን አራት ዋና ዋና ፈተናዎች ለመቋቋም መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት በምርጫ ጉዳይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ አራቱ የሀገሪቱ ፈተናዎችና ጠላቶች ተደርገው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገለጹት፡፡ ኮቪድ-19፣የበረሀ አምበጣ፣የዓባይ ጉዳይ እና ከኮቪድ ጋር ተያይዞ የኢኮኖሚ ጉዳይ ናቸው፡፡
“በመንግስት በኩል በከፍተኛ ጥረትና ትጋት ዜጎችን ለመታደግና የመጣብንን ጠላት ለመዋጋት እጅግ ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መንግስታቸው ከኢትዮጵያ ህዝብና ከዓለም መንግስታት በግልጽ ምስጋና እንደተቸረው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ አንድም መንግስት በዚህ ልክ እንዳሁኑ የተደራረበ ፈተኛ ያጋጠመው የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የምርጫ ጉዳይን ለአብነት አንስተዋል፡፡ የምርጫ ጉዳይን በተመለከተም “በኢትዮጵያ መንግስታት ታሪክ ምርጫ እንደአሁኑ አጀንዳ ሆኖ አያውቅም፤ ወይ አልነበረም ካለም ለይስሙላ የሚደረግ እንጂ የሚያጨቃጭቅ ጉዳይ አልነበረም” ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ምርጫ ብዙም አጀንዳ እንዳልነበረ ለማሳየትም “ከኤርትራ ጋር እየተዋጋንም ማድረግ ይቻል ነበር ፤ የሚፎካከር ኃይል ስላልነበረ፡፡ ግማሹ አውሮፓ ናቸው ግማሹ ኤርትራ ነው የነበረው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ግን በውጭ ሀገራት ያሉ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰባሰባቸው ምርጫ በጉጉት የሚጠበቅ እንዲሆን አድርጓል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፡፡
ወቅታዊዉን የሀገሪቱን ፈተና ቀለል አድርገው እንደማይመለከቱም የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የገጠሙንን ፈተናዎች ሁሉ በተቻለ መጠን በውይይትና በምክክር ፈትተን ኢትዮጵያን ማሻገር፣ የህዝቦቿን ደህንነት መጠበቅ ቀዳሚ ዓላማ አድርገን ነው የወሰድነው” ብለዋል፡፡
በተለይም በኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ በአጽንኦት ያብራሩ ሲሆን ከኮቪድ-19 ክስተት በኋላ ከተለያዩ አጋዥ አገሮች እና ተቋማት ጋር በመደራደር ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ማግኘት እንደተቻለ አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስብራት እንዳያጋጥማት ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ከ ዜሮ በታች እስከ 10 በመቶ (-10%) በላይ የኢኮኖሚ ድቀት ያጋጥመናል የሚል ስጋት እንዳለባቸው ያወሱት ጠቅላዩ ኢትዮጵያ ግን ብዙ የሚያሳስብ ስጋት የለባትም ብለዋል፡፡ በኮቪድ-19 ምክንያት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ቢቀንስ እንጂ ከዜሮ በታች (ኔጌቲቭ) ውስጥ እንደማይገባ የአይ.ኤም.ኤፍ፣ የዓለም ባንክ እንዲሁም የሌሎች የገንዘብ ተቋማት ትምበያ እንደሚያሳይም ጠቁመዋል፡፡ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳያጋጥም በተለየ መልኩ እየሰሩ ካሉ ጥቂት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗንም በማብራራት፡፡
“የኢኮኖሚ ቀውስ ሲያጋጥም፣ በውጭ ተጽዕኖ የሚከሰት በመሆኑ፣ በኢኮኖሚ ፎርሙላ (ቀመር) ብቻ አይፈታም” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ በመሆኑም ማክሮ ኢኮኖሚውን ለመታደግ የሚያስችሉ ሁለገብ ስራዎች በጥበብ እየተከናወኑ ነው፣ይሄም ዉጤት በማምጣት ላይ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
“በሚዲያ” አልያም “በሚስጥር” ከህወሓት ጋር ለመወያየት ዝግጅ ነኝ-ብልጽግና
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብልጽግና ፓርቲ (ብልጽግና) ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ጋር በአደባባይም ሆነ በሚስጥር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን ገለፁ፡፡
ብልጽግና በሚዲያ ወይም በሚስጥር ከህወሓት ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑና ህወሓትም በሚመራው ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን መብት ማክበር እንዳለበት የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ያሉት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት “ምርጫ 2012” በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ ባለመቻሉ ሊወሰዱ በሚችሉት አማራጮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አዲስዓለም ባሌማ ላነሱት ሀሳብ ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡
አቶ አዲስዓለም ባሌማ “የዚህ አመት ምርጫ አሁን ኮሮና መጣ እንጅ መጀመሪያም ሲልከሰከስ ነበር የመጣው፤ ያው መንግስትም በሙሉ ልብ ምርጫውን አካሂዳለሁ ብሎ ይዞ ሲገፋው ነው የነበረው፣ የቆየ ነገር አልነበረም፡፡ ከመጀመሪያውም ቢሆን ያዝ ለቀቅ ነበር፤መንግስት በዚህ ላይ ጠንካራ አቋም አልነበረውም” ሲሉ ነበር አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ“ብልጽግና ምርጫው አይደረግም የሚል እምነትም፣ ፍላጎትም የለውም፤ ቀደም ሲል አህአዴግ በነበረበት ጊዜ በስራ አስፈፃሚ በተሰበሰብንበት ሰዓት ምርጫው ይደረግ ተብሎ ሲወስንም እርሶ [አቶ አዲስአለም] ነበሩበት፤ አብረን ያያነው ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት “መንግስት ከመጀመሪያውኑ አቋሙ የተለሳለሰ ነበር የሚለው ተቀባይነት አይኖረውም፡፡”
ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ ጠንካራ መንግስት እንዲፈጠር የተለየ የውይይት “አሬንጅመንት/ስርአት”ያስፈልጋል ያሉት አቶ አዲስ አለም “ብልጽግና ፓርቲ ብቻውን ልምራው ካለ ውጤቱ ወደ ከፋ ችግር ይከተናል የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል፡፡
ለ27 አመታት ኢትዮጵያን ሲመራ የነበረው ግንባር ፓርቲ ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ሲመሰረት፣ የፓርቲው አባል የነበረው ህወሓት ‘አልዋሃድም’ ካለ በኋላ፤ ብልጽግናና ህወሓት አለመግባባት ውስጥ ገብተዋል፡፡
በፌደራል መንግስት በኩልም ችግር ካለ “ከፈለጋችሁ በሚዲያ፣ ከፈለጋችሁ በሚስጥር ለመወያየት ዝግጁ ነን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
“እናንተ [እነ አዲስአለም] በምትመሩት ክልል [ትግራይ ክልል] የሚፎካከሩ ፓርቲዎች”ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውንና ህወሓት ዲሞክራሲያዊ ድርጅት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
“እዛ እያዳፈንን እዚህ እንወያይ ግን አይሰራም፡፡ ዲሞክራሲ ‘ደብል ስታንዳርድ’ [ሁለት አይነት አሰራር] የለውም”፡፡
’የሽግግር መንግስት ይቋቋም‘ን በተመለከተ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀረቡት አማራጮች ከተሰጡ አስተያየትና ሃሳቦች በመነሳት ‘የሽግግር መንግስት ይቋቋም ሃገራዊ መግባባት ያስፈልጋል’ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
የሽግግር መንግስት ሊቋቋም ይገባል ብለው አቋም የያዙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አቋማቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ ነግርግን ብልጽግና ፓርቲ“የሽግግር መንግስት ይቋቋም” የሚለውን ሀሳብ አይቀበለውም፡፡
“የሽግግር ሳይሆን የብጥብጥ መንግስት ነው የምለው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንኳን በጋራ መንግስት ለመሆን በጋራ ምክር ቤት ተወያይቶ አጀንዳ መወሰን ያልቻለ ስብስብ በዚህ [ክሪቲካል] ወሳኝ ጊዜ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ቀልድ መቀለድ አያፈልግም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከዚህ ከወጣችሁ ከአንድ ሰዓት በኋላ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ምን እንደሚያጋጥም ምንም እውቀት የለንም” ያሉም ሲሆን “ዝም ብሎ ዘሎ ስልጣን መያዝ የሚቻልበትን መንገድ ከምንከተል በተቻለ መጠን ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ፣ነጻ እና ብዙ [አክተርስ] ተዋናዮች ያሉበት ማድረግ፤እንደ ተዋናዮቹ ቁጥር በመንግስትም በሌሎች ጉዳዮችም በጋራ የምንወስንበትን መንገድ መፍጠር” እንደሚበጅ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ከአሁን ቀደም ሲጠየቅ እንደነበረው ሁሉ ፓርቲዎች በፖሊሲና በርዕተ ዓለም ከሚቀራረቧቸው ፓርቲዎች ጋር ቢሰባሰቡ እንደሚበጅም ነው የተናገሩት፡፡
ይህ ቢሆን “በዚህ (በምርጫ) ጉዳይ ብቻም ሳይሆን በስልጣን ጉዳይም ቢሆን መደራደር” ችግር እንዳልነበረውም ተናግረዋል፡፡
“…አጀንዳ ይዛችሁ ኑ”
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ “የተሻለ ጊዜ ሲገኝ” የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለውይይት እንደሚጋብዙ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲዎቹ ዋና ዋና የሚሏቸውን አጀንዳዎች ይዘው እንዲመጡም ጠይቀዋል፡፡ አጀንዳዎቹ በፌዴራል፣በህገመንግስት፣ብሄራዊ መግባባት እና በሌሎችም ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይቱ የመንግስትና የተፎካካሪዎች እንዳይሆን ከተወያዮቹ መካከል በሁሉም ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ኮሚቴን በማዋቀር እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡ ኮሚቴው ምሁራንን እያወያየ፣ሰነድ እያዘጋጀ እንዳስፈላጊነቱ ለውይይት እያቀረበ ሊቀጥል እንደሚችልም ነው የገለጹት፡፡
ቅድሚያ የሚያስፈልጋቸውን አጀንዳዎች በመለየትና በማደራጀት ለኢትዮጵያ የሚፈይድ ሀሳብን ለማንሸራሸር ይጠቅማልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡