የኢትዮጵያ መንግሰት ኤች አር 6600 ረቂቅ ህግ እንዲዘገይ ስለመደረጉ እንደማያውቅ ገለጸ
ኤች አር 6600 በአሜሪካ ኮንግረስ ታገደ የሚል መረጃ ሲዘዋወር ነበር
የአሜሪካ ኮንግረስ ኤችአር 6600 ረቂቅ ህግ በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለማስቆም የሚያስችል እንደሆነ ይገልጻል
የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካው ኤች አር 6600 ረቂቅ ህግ በሂድት ላይ ስለመሆኑ እንጅ ከመጽደቅ እንዲዘገይ ስለመደረጉ እንደማያውቅ ገልጿል፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ያመጣል፤ግጭቱ እንዲቆም ያደረጋል የተባለው ረቂቅ ህግ በአሜሪካ ኮንግረስ ታግዷል የሚል መረጃ ሲዘዋወር ነበር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በጎንደር ከተማ በሰጡት መግለጫ ረቂቅ ህጉ እንዲዘገይ ወይም እንዳይጸድቅ መደረጉ አልተረጋገጠም ብለዋል፡፡ አምባሳደሩ እንዲዘገይ ተደርጓል የሚለውን መረጃ ማዘናጊያ እድርገው እንዲሚወስዱት ተናግረዋል፡፡
ረቂቅ ህጉ ለኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት አይጠቅም ያሉት አምባሰደሩ ኢትዮጵያ ረቂቅ ህጉ እንዳይጸድቅ የሚያደርጉትን ተቃውሞ አጠናክረው እደንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ረቂቅ ህጉ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነት እና ሌሎች ግጭቶችን፤ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን፣ የጦር ወንጀሎችን፣በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን፤ የዘርማጥፋትን እና ሌሎች ግፎችን ለማስቆም ሁሉንም የዲፕሎማሲያዊ፣የልማት እና የግህ መሳሪያዎች ይጠቀማል ይላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ህጉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት፤ የጦር ወንጀል፣ ዘር ማጥፋትን እና ሌሎች ግፎችን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥረት ያደርጋል፡፡
ይህ ረቂቅ ህግ እንዳይጸድቅ ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰማ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ጠይቋል፡፡