ሱዳን፤ በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ወደ ተመድ ሰብዓዊ መብቶች ም/ቤት ለመሄድ ማሰቧን ገለጸች
የግብፅና የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በግድቡ ዙሪያ የመንግስታቱ ድርጅት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል
የተመድ ፀጥታው ም/ቤት የግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት በተጀመረው አደራዳሪነት መቀጠልን እንደሚደግፍ ገልጿል
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሱዳን ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለመውሰድ ማሰቧን አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል ሳዲቅ አል ማህዲ ሀገራቸው በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድጋሚ ለመሄድ ማሰቧን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ሶስቱ ሀገራት በግድቡ ዙሪያ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈርሙ የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ኃላፊነቱን ይወጣል ብለው እንደሚጠብቁ ለሩሲያው የዜና ወኪል ስፑትኒክ ዘግቧል።
ይሁንና የተመድ ጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚና ተለዋጭ አባላት የሕዳሴ ግድብን አለመግባባት የአፍሪካ ሕብረት በጀመረው የአደራዳሪነት አግባብ እንዲቀጥል መናገራቸው ይታወሳል።
የኒውዮርኩ ተቋም ጉዳዩ በአዲስ አበባው ተቋም እንዲታይ አስተያየቶች የተሰጡ ቢሆንም፤ ካርቱም ግን አሁንም ዳግም ፊቷን ወደ አሜሪካ እያዞረች መሆኑ ተሰምቷል።
ግብፅ እና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት እንዲታይ በጠየቁት መሰረት ጉዳዩ በኒውዮርክ ታይቶ ነበር።
በዚህም መሰረት የግብፅ እና የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በግድቡ ዙሪያ የመንግስታቱ ድርጅት ጣልቃ እንዲገባ መየጠቃቸው የሚታወስ ሲሆን በውኃ፤ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትሯ የተወከለችው ኢትዮጵያ ደግሞ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በተጀመረበት በአፍሪካ ሕብረት ብቻ መሆን እንዳለበት ገልጻ ነበር።
የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚና ተለዋጭ አባላት፤ ከኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ የቀረበውን የአፍሪካ ሕብረትን አደራዳሪነት በመፍትሔ ሃሳብነት ማቅረባቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት መጀመሩን ግብፅና ሱዳን ከኢትዮጵያ የውኃ ሚኒስቴር መረጃ እንደደረሳቸው ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።