የአድዋ ድል ሲነሳ ደሴ ሙዚየም፣አንጎለላ፣ውጫሌ፣ወረኢሉና አድዋ ስማቸው የሚነሱ ቦታዎች ናቸው
የአድዋ ድል ሲነሳ ደሴ ሙዚየም፣አንጎለላ፣ውጫሌ፣ወረኢሉና አድዋ ስማቸው የሚነሱ ቦታዎች ናቸው
የአድዋ ጦርነትና የተገኘው ድል ሲነሳ በርካታ የሚወሱ ቦታዎች ያሉ ቢሆንም ዋና ዋና የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው፡፡
ደሴ ሙዚየም
ሙዚየሙ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ መውጫ በስተቀኝ የሚገኘውና በተለምዶ ዲቪዥን በመባል ከሚጠራው ቦታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከተደራጁ ሙዚየሞች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በሙዚየሙ ውስጥ ከአጼ ምንልክ ለንጉስ ሚካኤል የተበረከተው ስልክ፣ በአድዋ ጦርነት ጥቅም ላይ የዋሉ መሳሪያዎች እና በርካታ ውድ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡
አንጎለላ
አንጎላላ የአድዋ ጦርነት የመሩት የአጼ ምኒልክ የትውልድ ቦታ ነው፡፡አንጎለላ አድዋ ላይ ጣሊያንን ድል ያደረጉት የሆኑት ዳግማዊ አጼ ምንልክ እና ፊታውራሪ ገበየሁ(አባ ጎራው) የተወለዱባት ከተማ ናት፡፡
በአድዋ ጦርነት ሲፋለሙ የወደቁት የፊታውራሪ ገበየሁ አጽም ያረፈውም በከተማዋ በሚገኘው አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡
ውጫሌ
ለታሪካዊው የአድዋ ጦርነት መነሻ በመሆን ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የውጫሌ ውል ቀዳሚው ነው፡፡ የውጫሌ ውል በንጉሥ ምኒልክ እና በጣሊያን ንጉሥ ኡምቤርቶ ወኪል ኮንት ፔዮትሮ አንቶሎኒ መካከል በአሁኗ በአምባሰል ወረዳ ውጫሌ በምትባል ቦታ ሚያዚያ 25 ቀን 1881ዓ.ም የተደረገ የውል ስምምነት ነው፡፡
የውጫሌ ውል 20 አንቀጾች የነበሩት ሲሆን በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳው አንቀጽ 17 ነው፡፡ አንቀጽ 17 በአማርኛ “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግስት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል፡፡” የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም የኢትዮጵያ መንግስት ከፈቀደ ወይንም ከፈለገ በኢጣሊያ በኩል ከውጭ መንግስታት ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደሚችል የሚጠቅስ ነው፡፡
የአንቀጹ የጣሊያንኛ ትርጉም ግን “የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ አገር መንግስታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት አማካኝነት ማድረግ ይገባዋል፡፡” የሚል ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ይህ አንቀጽ ሉአላዊነትን የሚጥስ በመሆኑ ውሉ ይፍረስ ስትል ጥያቄ ብታቀርብም፣ በጣሊያን በኩል ተቀባይነት በማጣቱ የአድዋ ጦርነት ሊቀሰቀስ ችሏል፡፡
ወረኢሉ
ወረኢሉ በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ አንዷ ናት። ከተማዋ ቀደም ባለው ጊዜ ‹‹ዋሲል›› በመባል ትጠራ እንደነበረ ይነገራል፡፡ አንዳንዶች ግን የከተማዋን መመስረት ከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጋር ያገናኙታል፡፡
በታሪክ የወረኢሉ ስም ጎልቶ የሚነሳው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ለአድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ በአሳዋጁበት ጊዜ የሸዋ እና ደቡብ ሰራዊት በአንድ ማዕከል እንዲሰባሰብ የመረጧት ቦታ በመሆኗ ነው፡፡ በዘመኑ ለሰራዊቱ ትጥቅ እና ስንቅ ማዘጋጃ ማዕከል በመሆንም ለተመዘገበው ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡ ከታሪካዊነቷ አንጻር ሲታይ ወረኢሉ አሁንም ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ችግር እንዳለባት ይነሳል።
አድዋ
አድዋ በ1888 ዓ.ም ጦርነቱ የተካሄደበት ቦታ ሲሆን፤ ጦርነቱ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት በመጠናቀቁ ምክንያት በየአመቱ የድል በዓል የሚከበርበት ቦታ ነው፡፡ የአድዋ መልካምድራዊ አቀማመጥ ተራራማ ሲሆን፣ ይህም ለኢትዮጵያውያን አርበኞች ማሸነፍ ሚና እንደነበረው ታሪክ ያስረዳል፡፡ በአድዋ ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ጦር ካሸነፉበት ጊዜ አንስቶ አድዋና የአድዋ ድል በበርካታ ሀገራት በሚገኙ ጥቅር ህዝቦች ዘንድ የነፃነት ምልክት ሆነው ተወስደዋል፤ ለነፃነት ትግልም መነሳሳትን ፈጥረዋል፡፡