በኢትዮጵያ የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች አንድ ሊትር ቤንዚን እስከ 300 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች በጸጥታ ችግር ሳቢያ የነዳጅ ዋጋ ያሻቀበባቸው ክልሎች ናቸው
መተከል እና ካማሺ ዞኖች ነዳጅ አከፋፋዮች ስራ ካቆሙ ሁለት ዓመት አልፏቸዋል
ነዳጅ የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ከሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች መካከል ዋነኛው ነው። በዓለማችን የሚካነወኑ ማናቸውም ክስተቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ ከሚደረግባቸው ምርቶች መካከል ዋነኛው ነው ነዳጅ።
በኢትዮጵያም የነዳጅ ነገር አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል። ችግሩ በተለይም የጸጥታ ችግሮች ባለባቸው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች የነዳጅ እጥረቱ እና እሱን ተከትሎ የሚከሰቱ ጉዳቶች ከፍተኛ ናቸው።
አልዓይን አማርኛ የጸጥታ ችግሮች ባሉባቸው ክልሎች ህይወት እንዴት ቀጥሏል? ሲል ጠይቋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይም ካማሺ እና መተከል ዞኖች በአንጻራዊነት የጸጥታው ችግር የከፋባቸው ዞኖች ሲሆኑ፤ በሁለቱ ዞኖች የጸጥታ ችግሩ ከተፈጠረ ሁለት ዓመት አልፎታል።
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሁለት የዙኑ ነዋሪዎች እንዳሉት በዞኖቹ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ችግር አለ። ይህ በመሆኑ ምክንያት የሸቀጣሸቀጦች ዋጋ በእጅጉ ንሯል ብለውናል።
ነዳጅ እያገኘን ያለነው ከአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችአዋሳኝ ወረዳዎች በህገወጥ መንገድ ከሚነግዱ ነዳጅ ነጋዴዎች ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በጸጥታው ችግር ምክንያት ከሞተር ውጪ ሌሎች ተሸከርካሪዎች አይንቀሳቀሱም።
አብዛኞቹ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ያሉት በሞተር ነው። አንድ ሊትር ቤንዚንም ከ200 እስከ 300 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑንም ነዋሪዎች ለአል ዐይን ተናግረዋል።
ሌላኛው የጸጥታ ችግር ያለበት አካባቢ አፋር ክልል ሲሆን በተለይም ከህወሃት ሀይሎች ጋር ውጊያ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች እና ዙሪያ አንድ ባለ 25 ሊትር ቤንዚን እስከ 10 ሺህ ብር ወይም አንድ ሊትር ቤንዚን ከ300 ብር በላይ በመሸጥ ላይ መሆኑን ከነዋሪዎች ሰምተናል።
ሌላኛው የጸጥታ ችግር ካለባቸው ክልሎች መካከል አንዱ የሆነው የኦሮሚያ ክልል ሲሆን በተለየም በአራቱ የወለጋ ዞኖች የነዳጅ ችግሩ የተባባሰባቸው አካባቢዎች ናቸው።
አል ዐይን አማርኛ ያናገረው የነቀምቴ ከተማ የባለ ሶስት እግር (ባጃጅ) አሽከርካሪ በከተዋም ይሁን በዙሪያ ቤንዚን ማግኘት አዳጋች እንደሆነባቸው ይናገራል።
አሁን ላይ ግለሰቦች ነዳጅን ከባኮ አሊያም ከአርጆ ከተሞች በህገ ወጥ መንገድ በጄሪካን እየቀዱ እያመጡ እንደሚሸጡ የተናገረው አሽከርካሪው፤ እሱንም ቢሆን በውድ ዋጋ እንደሚሸጡት ነግሮናል።
በከተዋማ ውስጥ ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ በባለ ሁለት ሊትር የውሃ መሸጫ (ሃይላንድ) ጠርሙስ እየተደረገ በየመንደጉ እንደሚሸጥም አሽከርካሪው አሳውቋል።
ለከተማዋ በተቀመጠው ታሪፍ መሰረት አንድ ሊትር ቤንዚን በ34 ብር መሸጥ ሲገባው በህገ ወጥ መንገድ አንድ ሊትር በ110 ብር እና ከዛ በላይ ዋጋ እንደሚገዙትም ተናግሯል።
ወደ ከተማዋ ባሉ የነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ ከመጣ ሰነባብቷል፤ የግድ ኑሮን ለመግፋት ሲባል ቤንዚን በህገ ወጥ መንገድ ከሚሸጡ ሰዎች እየገዙ እየሰሩበት እንደሆነም አስታውቋል።
ቤንዚን ጭራሱኑ መጥፋቱን ተከትሎ በከተማዋ ውስጥ በቤንዚን የሚሰሩ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ስራ አቁመው እና ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ተቸግረው አንደነበረም ያስታውሳል።
ችግሩ ምንድን ነው በሚል አል አይን ጥያቄ ያቀረበለት አሽከርካሪው፤ የከተማዋ አስተዳደር አንድ ጊዜ ሰብስቧቸው “ቤንዚን አላመጣ ያሉት የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ናቸው፤ ይህ ተግባራቸውን አውግዟቸው” ብሎ እንደነበረ ይገልጻል።
የነዳጅ ማከፋፈያ ባለቤቶች ደግሞ በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር የተነሳ በነዳጅ አመላላሽ ቦቴ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ነዳጅ ማቅረብ እንዳቆሙ አሽከርካሪው ነግሮናል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም በበኩላቸው በኢትዮጵያ በቂ የነዳጅ መጠን ወደ አገር ውስጥ ገብቶ በነዳጅ አከፋፋዮች በኩል በየአካባቢው በመከፋፈል ላይ ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና የጸጥታ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች የነዳጅ አከፋፋዮች ነዳጅ ማከፋፈል አለመቻላቸውን እንደሚያውቁ ገልጸው፤ በቀጣይ የጸጥታው ሁኔታ ሲስተካከል ነዳጅ በታሪፉ ማግኘት ይጀምራሉ ሲሉ ተናግረዋል።