ሩሲያ በዩክሬን ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ ደረሰ
የስንዴ እና የበቆሎ ገበያዎችም የ5 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል
“የአውሮፓ የዳቦ ቅርጫት”በመባል የምትታወቀው ዩክሬን የዓለማችን ሁለተኛዋ የእህል እና የሱፍ አበባ ዘይት ላኪ መሆኗ ይታወቃል
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች በኋላ የነዳጅ ዋጋ በበርሚል 105 ዶላር መድረሱን ተሰማ፡፡
ጭማሪው ባለፈው ሰባት ዓመታት ከተስተዋሉ ጭማሪዎች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ መሆኑንም ነው የተገለጸው፡፡
- ሩሲያ በዩክሬኗ ዶንባስ ክልል ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ መጀመሯን አስታወቀች
- የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦራቸውን ወደ ሩሲያ እንዲመልሱ ተማፀኑ
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ በዩክሬን የተፈጠረው ሁኔታ በርካታ የዓለም አክሲዮናች ከስሯል እንዲሁም የወርቅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የዩክሬን ትርምስ ከነዳጅ ባሻገር ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ መስተጓጎል መፍጠሩንም የብሉምበርግ መረጃ ያመለክታል፡፡
በዚህም ሩስያ ወደ ዩክሬን መግባቷንና በዚህም ወደቦች እና የባቡር ሀዲዶች መዘጋታቸውን ተከትሎ የምግብ ምርቶች የሚጫኑባቸው የትራንስፖርት ማሽነሪዎች ለመቆም ተገዷል ተብለዋል፡፡
የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻን ተከትሎ እስካሁን ወደቦቿ መዘጋታቸውንና ነጋዴዎች እቃዎቻቸውን ወደ ሀገሪቱ ወደቦች ለማዘዋወር እና ለማውጣት መርከቦችን መጠቀም አለመቻላቸው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡
የለም አፈር ሀገር እንደሆነች የሚነግርላትና “የአውሮፓ የዳቦ ቅርጫት” በሚል ቅጽል ስም በምትታወቀው ዩክሬን ሁለተኛዋ ትልቁ የዓለም እህል እና ዋና የሱፍ አበባ ዘይት ላኪ መሆኗ ይታወቃል፡፡
ሀገሪቱ የምታመርታቸው ምርቶች ለማንቀሳቀስ የባቡር እና የወደብ መሠረተ ልማት የሚያስፈልጋቸው ግዙፍ እቃዎች እንደሆኑም ይነገራል።
ሩሲያ ወተደራዊ ዘመቻ ከመጀሯ በፊት ሁኔታው ያሰጋቸው አንዳንድ የአውሮፓ ባንኮችም በሩሲያ እና በዩክሬን የሸቀጦች ንግድ ላይ ገደብ ሲጥሉ ቆይቷል፡፡
እንደተሰጋው አልቀረም አሁን ላይ ሩሲያ በዩክሬን ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ ወሳኝ የግብርና ምርቶቸ ላይ የዋጋ ንረት እየተስተዋለ ነው፡፡
የስንዴ እና የበቆሎ ገበያዎች በቺካጎ ልውውጥ በሚፈቀደው ከፍተኛ መጠን ጨምረዋል፣ የሁለቱም ሰብሎች ዋጋ ከ5% በላይ እየላቀ ሲሆን በፓሪስ ያለው የስንዴ ዋጋ በ16 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በጥቁር ባህር (Black Sea) እና በሌሎች ቦታዎች ላይ ያሉ የሩሲያ ወደቦች የተለመደ እንቅስቃሴ ቢኖርም፤በአዞቭ ባህር ውስጥ የነበረው የመርከብ ጭነት አገልግሎት መቆሙ የሩሲያ የፌደራል ወንዝ እና የባህር ውስጥ ትራንስፖርት ኤጀንሲ አስታውቋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬኗ ምስራቅ ዶንባስ ክልል ጦራቸውን በማስማራት ለዩ ወታደራዊ ዘመቻ ማስጀመራቸው ትናት ምሽት በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ዛሬም ቀጥሎ የዋለው ወታደራዊ ዘመቻ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዋና አጀንዳ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡