ኢትዮጵያ በቱርክ በመሬት መንቀጥቀጥ ለተጎዱ ሰዎች የቁሳቁስና የነፍስ አድን ቡድን መላኳን ጠ/ሚ ዐቢይ አስታወቁ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቱርክና ሶሪያ የሰብዓዊ እርዳታ የማጓጓዝ ዘመቻን መቀላቀሉን አስታውቋል
በቱርክ እና በሶሪያ በሳለፍነው ሳምንት በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ43 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል
ኢትዮጵያ በቱርክ በመሬት መንቀጥቀጥ ለተጎዱ ሰዎች የቁሳቁስና የነፍስ አድን ቡድን መላኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
በቱርክ እና በሶሪያ ከሳምንት በፊት በደረሰ የርዕደ መሬት አደጋ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ጻቸው ባጋሩት መልእክት፤ ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሴፕ ታይፕ ኤርዶጋን ጋር በስልክ መወያየታቸውን አስታውቀዋል።
- የቱርክ እና ሶሪያን ርዕደ መሬት የተነበየው ሆላንዳዊ ቀጣይ ተረኞቹ እነማን ናቸው አለ?
- 22 የኤምሬትስ አውሮፕላኖች በርዕደ መሬት ለተመቱት ሶሪያና በቱርክ እርዳታ አደረሱ
በዚህም “በቱርክ በመሬት መንቀጥቀጥ በጠፋው የሰው ሕይወት እና በወደመው ንብረት የተሰማኝን ጥልቅ ኀዘን ለፕሬዝዳንት ሬሴፕ ታይፕ ኤርዶጋን ገልጫለሁ” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ የተቸገረ ወዳጇን ለመርዳት ምንጊዜም ቁርጠኛ ናት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ባላት ዐቅምም የቁሳቁስ እና የነፍስ አድን ቡድን ለቱርክ አበርክታለች” ሲሉም አስታውቀዋል።
በተያያዘ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በቱርክ እና ሶሪያ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ የሚደረገውን ዘመቻ መቀላቀሉን አስታውቋል።
በዚህ መሰረትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አውፕላኖች ከሜክሲኮ በአደጋው ተጎጂ ለሆኑ ቱርካውያን የተደረገውን 100 ቶን የሰብዓዊ እርዳታ እያጓጓዙ መሆኑን ከአየር መንገዱ አስታውቋል።
በቱርክ እና በሶሪያ ከሳምንት በፊት በደረሰ የርዕደ መሬት አደጋ ከ43 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ በርካቶች ደግም ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው ይታወቃል።
በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው እስካሁን በቱርክ ብቻ የ38 ሺሀ 44 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ በሶሪያ ደግሞ 5 ሺህ 800 ሰዎች ሞተዋል።