22 የኤምሬትስ አውሮፕላኖች በርዕደ መሬት ለተመቱት ሶሪያና በቱርክ እርዳታ አደረሱ
እርዳታው በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች 640 ቶን እርዳታና የፍለጋና የህይወት አዳኝ ቡድኖችን ያካተተ ነው
ሀገሪቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ልዩ የግንኙነት ማዕቀፍና ለተጎጂዎች የመደረስ ተነሳሽነት እጇን መዘርጋቷን አስታውቃለች
22 የኤምሬትስ አውሮፕላኖች በርዕደ መሬት ለተመቱት ሶሪያና በቱርክ እርዳታ አደረሱ
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሶሪያና በቱርክ ለተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ተጎጂዎች የእርዳታ እጇን ዘርግታለች።
ኤምሬትስ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ለመደገፍ በሀገሪቱ መሪዎች መመሪያ መሰረት 640 ቶን የሚመዝን እርዳታ እስከ ትናንት ሀሙስ ልካለች።
ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈር ቀዳጅ የሰብአዊነት ሚናዎች የምትወጣና ለአስርት ዓመታት እጇን በመዘርጋት ትታወቃለች።
ለሰሞነኛው የርዕደ መሬት አደጋ ተጎጂዎችም በ22 በረራዎችን እርዳታዎችን አቅርባለች።
እስካሁን ወደ ሶሪያ በሰባት በረራዎች የሰብዓዊ እርዳታዎችን ጨምሮ የምግብ እቃዎችንና ለተጎዱት መጠለያ 515 ድንኳኖችን አድርሳለች።
የተጎዱ የቱርክ ህዝቦችን ለመታደግ ደግሞ እስካሁን የፍለጋና የህይወት አዳኝ ቡድኖችን ጨምሮ በ15 በረራዎች ተንቀሳቃሽ ሆስፒታልን አድርሳለች ነው የተባለው።
ሆስፒታሉ የድንገተኛ እና የቀዶ ጥገና ክፍሎችን ያካትታልም ተብሏል።
እርዳታው 50 አልጋዎች አቅም ያላቸው ታካሚ ክፍሎች፣ ላቦራቶሪ እና ፋርማሲ፣ ኤክስሬይ እና ሲቲ አገልግሎቶች በተጨማሪ የአጥንት ህክምና፣ አጠቃላይ የቀዶ ህክምና፣ ማደንዘዣ፣ ከፍተኛ እንክብካቤ እና ልዩ የህክምና ቡድኖች ከተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች የተውጣጡ ባለሞያዎችን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ልዩ የግንኙነት ማዕቀፍ እና በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አደጋዎች ለተጎዱ እርዳታ በመስጠት ለሰብአዊነት የምትጫወተው ሚና አካል መሆኑ ተነግሯል።