ቱርክ ከርዕደ መሬቱ ጋር በተያያዘ የግንባታ ተቋራጮችን በቁጥጥር ስር ማዋል ጀመረች
በ131 ተቋራጮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ያወጣችው አንካራ፥ ከሀገር ሊወጡ የነበሩ የግንባታ ተቋራጮችን መያዟን አስታውቃለች
ቱርክ አደጋ የሚቋቋሙ ህንጻዎች እንዲገነቡ የሚያስገድድ የግንባታ ህግ ቢኖራትም ተፈጻሚነቱ እምብዝም ነው ተብሏል
በቱርክ በ10 ግዛቶች ባለፈው ሳምንት የደረሰው ርዕደ መሬት ከ6 ሺህ በላይ ህንጻዎችን አፈራርሷል።
የህንጻዎቹ መፈራረስ በውስጣቸው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ እስካሁንም በፍርስራሾች ውስጥ የሚገኙት በርካት ናቸው እየተባለ ነው።
ይህ አሰቃቂ አደጋ የበርካቶችን ህይወት እንዲቀጥል የህንጻዎቹ የግንባታ ጥራት አንዱ ምክንያት ነው ያለችው ቱርክ፥ የግንባታ ተቋራጮችን በቁጥጥር ስር ማዋል ጀምራለች።
- አረብ ኢምሬት በአንድ ቀን ውስጥ 117 ቶን ምግብ ወደ ቱርክ እና ሶሪያ ላከች
- በርዕደ መሬቱ የተጎዱ ዜጎችን ህይወት የማትረፉ ተግባር አድካሚ እየሆነ መምጣቱን የነፍስ አድን ሰራተኞች ገለጹ
ለፈራረሱት ህንጻዎች ተጠያቂ ናቸው የተባሉ 131 የግንባታ ተቋራጮች የእስር ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ነው የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፉዋት ኦክታይ የተናገሩት።
ከእስር ማዛዣ ከወጣባቸው ውስጥም በአዲያማን ከተማ በርካታ ህንጻዎችን የገነቡ ሁለት ተቋራጮች ወደ ጆርጂያ ሊያመሩ ሲሉ በኢስታንቡል አውሮፕላን ማረፊያ መያዛቸው ተነግሯል።
በጋዚያንቴፕ ከተማ የፈራረሱ ህንጻዎችን የገነቡ ናቸው የተባሉ ሁለት የግንባታ ተቋራጮችም እንዲሁ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አናዶሉ አስነብቧል።
በሃታይ ግዛት አንታክያ ከተማ ባለ12 ፎቅ ህንጻ የገነባው ተቋራጭም ባለፈው አርብ ከሀገር ለመውጣት ሙከራ ሲያደርግ በኢስታንቡል አውሮፕላን ማረፊያ መያዙ የሚታወስ ነው።
የቱርክ ፍትህ ሚኒስቴር “የርዕደ መሬት ወንጀል ምርመራ” ቢሮ አቋቁሞ ከግንባታ ጋር የተያያዙ ህገወጥ ተግባራት የፈጸሙ አካላትን ለህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ትናንት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚህም ከፈራረሱት ህንጻዎች ላይ ናሙናዎች እየተወሰዱ የግንባታ የጥራት ደረጃዎች ይፈተሻሉ፤ ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙትም ተገቢው እርምጃ ይወሰድንባቸዋል ተብሏል።
የስነህንጻ፣ የስነምድር እና ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎችም በዚሁ የማጣራት ስራ እንዲሰማሩ ትዕዛዝ ተላልፏል መባሉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ቱርክ በፈረንጆቹ 1999 ከደረሰውና ከ17 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በኋላ የግንባታ ህጓን ማጥበቋ ነው የሚነገረው።
ሀገሪቱ ርዕደ መሬት ደጋግሞ እንደሚጎበኛት ታውቆ አደጋውን የሚቋቋም ህንጻ መገንባት ተገቢ ቢሆንም ለሚመጣው አደጋ ዝግጁ የሆነ ህንጻ ግንባታ እንደሌለ ግን ባለፈው ሳምንት የደረሰው አደጋ አሳይቷል።
በ2018 የወጣው መረጃም ይህንኑ ነው የሚያረጋግጠው፤ በሀገሪቱ ከተገነቡ ህንጻዎች ግማሹ (13 ሚሊየን) ከተቀመጠው ደረጃ በታች የተገነቡ ናቸው።
ለዚህም የግንባታ ተቋራጮች በዋነኝነት ተጠያቂ የሚደረጉ ሲሆን፥ ለግንባታዎቹ ፈቃድ የሚሰጡ አካላት የቁጥጥር እና እርምጃ ማነሳም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይነሳል።
የቱርክ ግዙፍ ከተማ የሆነችው ኢስታንቡል በቅርቡ ተመሳሳይ ርዕደ መሬት እንደምታስተናግድ ይጠበቃል መባሉም የከተማዋን ነዋሪ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከቶታል ነው የተባለው።
ከአደጋው ሊተርፉ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ህንጻዎች ኪራይ ከባድ መሆኑም በርካቶች በሚያስፈሩት ህንጻዎች ውስጥ ሆነው የሚመጣውን እንዲጠባበቁ እንዳስገደዳቸው ይናገራሉ።
ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል የግንባታ ተቋራጮች ድርሻም ቀላል አይደለም ያለው የፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አስተዳደር በ131 ተቋራጮች ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቶ በቁጥጥር ስር እያዋለ ነው።